በሰሜን ኢትዮጵያ፣ በህወሓትና በፌዴራል መንግሥት መካከል በ2013 ዓ.ም. በተቀሰቀሰውና ለሁለት ዓመታት በቆየው ጦርነት ወቅት፣ ግብጽ ለህወሓት የፋይናንስ ድጋፍ ማድረጓን በወቅቱ የህወሓት ቃል አቀባይ የነበሩት አቶ ጌታቸው ረዳ ይፋ አደረጉ።
አቶ ጌታቸው አሁን ላይ የፌዴራል መንግሥት የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሆነው እያገለገሉ ናቸው።
ጦርነቱ በፕሪቶሪያ የዘላቂ ሰላም ስምምነት ከተቋጨ በኋላ፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ ጌታቸው፣ በህወሓት ውስጥ በተፈጠረው መከፋፈል ምክንያት ከድርጅቱ ወጥተው ስምረት የተባለ ፓርቲ መመሥረታቸው ይታወሳል።
በህወሓት ውስጥ ቁልፍ ሚና የነበራቸው አቶ ጌታቸው፣ ግብጽ ድጋፍ መስጠቷን ይፋ ያደረጉት ትናንት በኢትዮጵያ መከላከያ ኮሌጅና በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት በተዘጋጀው የፖሊሲ ውይይት ላይ ነው።
አቶ ጌታቸው ህወሓት ከግብጽ 500 ሚሊዮን ዶላር የፋይናንስ ድጋፍ ጠይቆ ማግኘት የቻለው ግን 500 ሺህ ዶላር ብቻ እንደነበር በዚሁ መድረክ ላይ ተናግረዋል። አቶ ጌታቸው የገንዘቡ መጠን አነስ ተደርጎ እንዲቀርብ ሐሳብ አቅርበው የነበረ ቢሆንም፣ በሊቀመንበሩ ተቀባይነት እንዳላገኘ ጠቅሰዋል።
ይህ የአቶ ጌታቸው ንግግር፣ ግብጽ ለህወሓት ድጋፍ ታደርጋለች የሚለውን በኢትዮጵያ የሚቀርበውን ክስ የሚያጠናክር ሆኗል።
ግብጽ፣ ሱዳንና ኤርትራ
አቶ ጌታቸው በአፍሪካ ቀንድና በኢትዮጵያ የጸጥታ ጉዳዮች ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ግብጽ፣ ኤርትራና ሱዳን ጸረ-ሰላምና ጸረ-ኢትዮጵያ ጥምረት ፈጥረዋል ሲሉ አጥብቀው ተችተዋል።
የኤርትራ መንግሥት በአገር ውስጥ ያሉ ታጣቂዎችን በመደገፍ የሚያደርገውን ተግባር የኮነኑት አቶ ጌታቸው፣ በሻዕቢያ የሚመራው የኤርትራ መንግሥት በተሳሳተ ስሌት ውስጥ መግባቱንና የኢትዮጵያ ጦር ድንበር አካባቢ መቅረቡ የህልውና ስጋት ውስጥ እንደከተተው ተናግረዋል።
ኤርትራ “ስትራቴጂክ ጥልቀት” እንደሌላት የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ የኢትዮጵያ አለመረጋጋትን ኤርትራ እንደ ደህንነት ጥቅም እንደምትመለከተው ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በዶክተር ደብረጽዮን የሚመራው ህወሓት የትግራይ ኃይሎች አባላት በሱዳን ዳማዚን አካባቢ ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጋር እየተዋጉ እንደሆነ የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ በአል-ቡርሃን የምትመራው ሱዳን በጸረ-ኢትዮጵያ ጥምረቱ ውስጥ እንዳለች ጠቅሰዋል።
አቶ ጌታቸው ግብጽም በተመሳሳይ በሱዳንና በኢትዮጵያ ውስጥ ትርምስ እንዲኖር እንደምትፈልግ ተናግረዋል። አባይ ወንዝ የሚያመነጨውን ውሃ አብዛኛውን ለግብጽ የሚሰጥ እንደሆነ የሚቆጠረውን “ታሪካዊ መብት” ለማስቀጠል እንደምትፈልግ ገልጸዋል።

አቶ ጌታቸው በኢትዮጵያ ውስጥ ትርምስ መኖር አገሪቱን ከተጨማሪ ልማት ስለሚያደናቅፍ፣ ግብጽ ይህንን እንደ ስትራቴጂያዊ ግብ እንደምትመለከተው ተናግረዋል።
ከአቶ ጌታቸው ንግግር በፊትም የፌዴራል መንግሥት ግብጽ፣ ሱዳንና ኤርትራ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ታጣቂዎችን እየደገፉ እንደሆነ በተደጋጋሚ ጊዜ ሲገልጽ ቆይቷል። ሆኖም ሦስቱም አገራት ይህንን ክስ ሲያስተባብሉ ቆይተዋል።
አቶ ጌታቸው ይህ ትብብር ያለ ስኬት መፍረሱንና ባለፈው ወር ያገረሸው ጦርነትም በፌዴራል መንግሥት ድል መጠናቀቁን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ቀይ ባሕርና አባይ ወንዝ
ኢትዮጵያ ከራሷ ተገንጥላ ነጻ አገር ከሆነችው ኤርትራ፣ ከሱዳንና ከግብጽ ጋር የተለያዩ ታሪካዊ ግንኙነቶች አሏት። የኤርትራ መገንጠልና ነጻ አገር መሆን ኢትዮጵያን ወደብ አልባ አገር አድርጓታል። ይህም በሁለቱ አገራት መካከል ለሦስት አስርት ዓመታት ገደማ “No peace, no war” በሚል የሚገለጽ፣ በኩርፊያ የተሞላ ግንኙነት እንዲኖር አድርጓል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የተሻሻለው የሁለቱ አገራት ግንኙነትም ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በኋላ እየተባባሰ ሄዶ፣ ባለፈው ወር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን በይፋ አቋርጠዋል።
ኢትዮጵያ ከግብጽና ከሱዳን ጋር ከአባይ ወንዝ ጋር በተያያዘ የቆዩ አለመግባባቶች እንዳሏት ይታወቃል።
ግብጽ፣ ሱዳንና ኤርትራ ጸረ-ኢትዮጵያ ትብብራቸውን ያጠናከሩት፣ ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባሕር መዳረሻ ማግኘትን የህልውና ጉዳይ አድርጋ ከመመልከቷና የቀይ ባሕር ዳርቻ ካላቸው አገራት ጋር በሰጥቶ መቀበል መርህ ወደብ ለማግኘት ድርድር እንደምትፈልግ ከገለጸች በኋላ ነው።
ሦስቱም አገራት በቅርቡ በግብጽ ባደረጉት ውይይት፣ የቀይ ባሕርን የማስተዳደር ጉዳይ የቀይ ባሕር ዳርቻ ባላቸው አገራት ብቻ መወሰን እንዳለበት የሚገልጽ የጋራ መግለጫ አውጥተዋል።
ይህንን ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአባይ ወንዝና በቀይ ባሕር ላይ የሚደረጉ ውይይቶች የኢትዮጵያን ሕጋዊ ጥቅሞች ከግምት የሚያስገቡ መሆን እንዳለባቸው በመግለጽ፣ የአገራቱን የጋራ መግለጫ በተዘዋዋሪ ተቃውሟል።











