የኢትዮጵያ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እንዳረጋገጠው በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ዝናን ያተረፈው የዓለም የኢንተርኔት ጉባኤ (World Internet Conference – WIC) በመስከረም 2019 ዓ.ም (September 2026) በአዲስ አበባ ይካሄዳል። ይህ ጉባኤ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቻይና ውጭ እንዲካሄድ ሲወሰን ኢትዮጵያ የዓለም የቴክኖሎጂ ኃያላን መድረክ እንድትሆን ዕድሉን አግኝታለች።
በቅርቡ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር በለጠ ሞላ እና የጉባኤው ምክትል ዋና ጸሐፊ ሚስተር ሊያን ሃኦ ባደረጉት ምክክር የቴክኒክ ዝግጅቶች መጀመራቸውን ገልጸዋል። ስብሰባው በዋናነት ሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI)፣ የሳይበር ደህንነት እና የዲጂታል ክፍተትን ማጥበብ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሲሆን እንደ ጉግል (Google)፣ ንቪዲያ (Nvidia) እና አሊባባ (Alibaba) ያሉ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ተቋማት እንደሚሳተፉበት ይጠበቃል።











