Loading...

አፍሪካ የትምህርት ዘርፏን ለማዘመን የቻይናን እውቀትና ችሎታ የራሷ ማድረግ ትፈልጋለች

የቻይናና አፍሪካ የትምህርት ዘርፍ ግንኙነት የተጀመረው እ.ኤ.አ. በ1950ዎቹ ነበር።ይህ የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንኙነት በፋይናንስና በሌሎች መሰናክሎች ምክንያት የተፈለገውን ያህል አልሄደም።

ይሁን እንጂ የቻይና-አፍሪካ ትብብር (ፎካክ) እ.ኤ.አ. በ2000 ከተቋቋመ በኋላ ትብብሩ ወጥነትና ተቋማዊነት እንዲኖረው በማድረግ የትምህርት ዘርፉ ትብብሩ እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ትምህርት በቻይናና አፍሪካ መካከል ቁልፍ የትብብር መስክ ሲሆን የአፍሪካ ተማሪዎች በቻይና ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የተለያዩ ፕሮግራሞችን ለማጥናት መጉረፍ ጀመሩ።

ለአፍሪካ ተማሪዎችና የመንግስት ሰራተኞች የሀገሪቱ መንግስት ባመቻቸው የዩኒቨርሲቲ ግንኙነቶችና በግል ብዛት ያላቸው የትምህርት እድሎች ተመቻቹ። በሀገራት የውስጥ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ ያለመግባትን ዋና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ መርህ ያደረገችው ቻይና ፈጣን የኢኮኖሚና የቴክሎጂ ልህቀት ላይ ስትደርስ የአፍሪካ መሪዎች እነዚህን ሞዴሎች ወደ ሀገራቸው የማምጣትና ተግባራዊ የማድረግ ጉጉት ሊያድርባቸው ችሏል።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ለአፍሪካ-ቻይና ግንኙነት እጅግ ትልቅ ቦታ በመስጠት ለዘርፉ ትብብር አስተዋጽኦ አድርጓል።በኮሚሽኑ የትምህርት ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት ሶፊያ ንዴሙቲላ እንደተናገሩት አፍሪካ የቻይናን እውቀትና ችሎታ መተግበር ትፈልጋለች።

“እውቀታቸውን መጠቀም እንፈልጋለን፤ ኢንዱስትሪያቸውን ማየት እንፈልጋለን። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማችንን በማጠናከርና በእነሱ ላይ በመጨመር ለአፍሪካ እንዲሆን አድርገን መተግበር እንፈልጋለን “ ብለዋል ኃላፊዋ።

የከፍተኛ ትምህርት፣የሙያና የቴክኒክ ስልጠና

በቅርብ የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከሆነ ቻይና የአፍሪካ ተማሪዎችን በመቀበል ቀዳሚ የነበሩትን አሜሪካን፣ እንግሊዝንና ፈረንሳይን በመብለጥ ቀደሚ መዳረሻ ሆናለች። ከኮቪድ ወረርሽኝ በፊት ፈረንሳይ 1ኛ ደረጃ ላይ ነበረች።

በቻይና ያለው የትምህርት ክፍያ ከምዕራባውያን ሀገራት ጋር ሲነጻጸር ዝቅ ያለ መሆኑና የቻይና በፖሊሲ የተደገፈ የመርሃግሮች(ፕሮግራሞች) መስፋፋት ለአፍሪካውያን ተማሪዎች አበረታች ሆነዋል። ፎካክ የትምህርት እድሎችን በማመቻቸት ለቻይና-አፍሪካ ግንኙነት በቁርጠኝነት ተንቀሳቅሷል።

በአሁኑ ወቅት ቻይና 50,000 አፍሪካውያን ተማሪዎችን በየአመቱ ትቀበላለች። እ.ኤ.አ. ከ2011-2017 በቻይና የሚመማሩ አፍሪካውያን ተማሪዎች ቁጥር 258 በመቶ ጨምሯል፤ ይህም በአሜሪካ ካለው የምዝገባ እድገት ዘጠኝ እጥፍ ፈጣን ነው። 350 የአፍሪካ የትምህርት ተቋማት ከቻይና ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በትብብር ይሰራሉ።

ቻይናና አፍሪካ በመካከላቸው ያለውን መስተጋብር የበለጠ ለማጠናከር ትብብራቸውን ወደ ቋንቋና ባህል አስፍተውታል።
የአፍሪካ መሪዎች በቻይና ኢንዱስትሪዎች ያዩትን እውቀትና ችሎታ ባልጠናው የአፍሪካ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይ መተግበር ይፈልጋሉ።
አፍሪካውያን የሙያና የቴክኒክ ስልጠናዎችም ቁልፍ የትብብር ዘርፎች እንዲሆኑ ትኩረት መስጠታቸው ተከትሎ ቻይና ለድጋፍ እጇን ዘርግታለች። ቻይና በአፍሪካ ለተግባር ስልጠና የሚውል ሉባን የተባለ ወርክሾፕ በማዘጋጀት፣ በሜካትሮኒክስ፣በባቡርና በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፉ ስልጠና ስትሰጥ ቆይታለች።

ደቡብ አፍሪካውያን ተማሪዎች በHangzhou Polytechnic, ቻይና (September, 2025)

ትብብርን ለማጠናከር የቋንቋና ባህል ልውውጥ

የኢትዮጵያና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በተለይም ለወጣት ዲፕሎማቶችና ተማሪዎች የማንዳሪን ቋንቋ ትምህርት በመስጠት እየተጠናከረ መሆኑን ምሁራንና ዲፕሎማቶች ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ እንደተናገሩት ወጣት ዲፕሎማቶችን ከቻይና ቋንቋ ጋር ለማስተዋወቅ የተደረጉ ጥረቶች ዘንድሮ 55 ዓመት የሆነውን ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሚያሳዩ ግልጽ ማስረጃዎች ናቸው። በዚህ መሠረት ዩኒቨርሲቲው ከ12 ዓመት በፊት የኮንፉሺየስ ኢንስቲትዩትን በመመስረት ያሳየውን ቁርጠኝነት በመቀጠል ከኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር (MoFA) እና ከቻይና ኤምባሲ ጋር በመተባበር ለዲፕሎማቶች ለመምህራን እና በኢትዮጵያ የኦሮሚያ ክልል ለሚገኙ አዳሪ ት/ቤት ተማሪዎች የቻይንኛ ቋንቋ ስልጠና እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል። እንደ እርሳቸው ገለጻ የዩኒቨርሲቲው የኮንፉሺየስ ኢንስቲትዩት በዲግሪ ደረጃ (ባችለር) ፕሮግራሞች እና በአጭር ጊዜ ስልጠና ኮርሶች የቻይንኛ ቋንቋ ትምህርት በመስጠት ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል።

የማንዳሪን ቋንቋን የሚማሩ አፍሪካውያን ተማሪዎች

ፕሬዚዳንቱ እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያና ቻይና “ጥልቅ የሆነ የባህላዊና ዲፕሎማሲያዊ ተመሳሳይነቶችን ይጋራሉ። ለነፃነታቸው ተዋግተዋል፤ የምዕራባውያን የበላይነትን ተቃውመዋል፤ የሰለጠነ ነፃ ሀገር ለመገንባት ተጋድለዋል።” ቻይና ለመበልጸግ አራት ዐሥር ዓመታት እንደወሰደባት የገለጹት ፕሬዝደንቱ ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ብልጽግናዋን ለማሳካት “የቻይናን መንገድ መከተል አለባት” ብለዋል።
የቋንቋ ብቃትና የባህል ግንዛቤ የዲፕሎማሲ ስራ እንደሚያቀል ግልጽ ነው። የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር (MoFA) ባልደረባ የሆኑት ባለስልጣንና እና የቻይንኛ ቋንቋ ስልጠና የወሰዱ ዲፕሎማት በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምስራቅና የፓሲፊክ ጉዳዮች ምክትል ጀነራል የሆኑት አምሀ ሀይለጊዮርጊስ የኢትዮጵያና ቻይና ግንኙነት ተለዋዋጭ የሆነውን የአለም ሁኔታ ተቋቁሞ ማበቡን ተናግረዋል።

ምክትል ዳሬክተሩ “ለምንም ተጽእኖ የማይንበረከክ” ሲሉ የገለጹት ይህ ግንኙነት በባህልና በቋንቋ ልውውጥ መጠናከሩን ገልጸዋል።
“በዚህ መንፈስ ነው ትልቅ አለምአቀፍ ጠቀሜታ ያለውን የማንደሪን ቋንቋ ለዲፕሎማቶቻችን ማስተማር አስፈላጊ የሆነው። ማንደሪን ከመግባቢያ በላይ ነው፤ የቻይናን ልብ፣አስተሳሰብና ስልጣኔ  ለመረዳት የሚያስችል መግቢያ በር ነው” ብለዋል አምሀ።

የቻይንኛ ቋንቋ ኮርስ የተማረችው የኢትዮጵያ ዲፕሎማት ማክዳ አማረ እንደተናገረችው ለዲፕሎማቶች ቋንቋውን መማር ችሎታን ለማዳበር ብቻ ሳይሆን ከቻይና ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ወሳኝ ነው።

ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት በተከፈቱ የኮንፉሽየስ ኢንስቲትዩቶች የማንደሪን ቋንቋ እየተሰጠ ሲሆን በቻይና ዩኒቨርሲቲዎችም በተመሳሳይ የአፍሪካ ቋንቋዎችን እያስተማሩ ይገኛሉ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኮንፉሺየስ ኢንስቲትዩት (Confucius Institute)

Share this article

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው