በመካከለኛው ምስራቅ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ማስቆም የሚችሉት የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ብቻ ናቸው ያሉት የግብጹ ፕሬዝደንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ የነዳጅ ዋጋ በበርሜል ከ200 ዶላር በላይ ሊያሻቅብ ይችላል የሚለው ስጋት የተጋጋነ አይደለም ብለዋል።
ሲሲ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከእስራኤል ጋር በመቀናጀት በኢራን ላይ እያካሄዱ ያሉትን ጦርነት እንዲያቆሙ አሳስበዋል።
“በቀጠናችን፣ በአረብ ባህረሰላጤ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ማንም አያስቆመውም፣ አንተነህ(ትራምፕ) የምታስቆመው” ሲሉ ሲሲ በካይሮ በተካሄደው የግብጽ የ2026 ኢነርጂ ሾው ስብሰባ ላይ ተናግረዋል።
ለረጅም ጊዜ ከአሜሪካ ወታደራዊ እርዳታና ከሀብታም የባህረሰላጤው ሀገራት ድጋፍ ስታገኝ የቆየችው ግብጽ፣ ኢራን በባህረሰላጤው ሀገራት ላይ እየሰነዘረች ያለውን ጥቃት በማውገዝ ግጭቱ የበለጠ እንዳይስፋፋ የዲፕሎማሲ ጥረቶች እንዲሳኩ እየገፋች ነው።
ሲሲ ግጭቱ የነዳጅ ዋጋ እንዲጨምርና አቅርቦት እንዲቀንስ ስለሚያደርግ ውጤቱ የከፋ እንደሚሆን ተናግረዋል።
“በማምረቻ ወይም በማጣሪያ የኢነርጂ መሰረተልማቶች ላይ የሚሰነዘረው ጥቃት በአለምአቀፍ ኢኮኖሚና በነዳጅ ዋጋ ላይ ከባድ ችግር እንዳያስከትል እፈራሉ” ብለዋል ሲሲ። ሲሲ አክለውም የአለምን ገበያ የሚከታተሉ “የአንድ በርሜል ነዳጅ ዋጋ ከ200 ዶላር በላይ ከፍ ሊል እንደሚችል አስጠንቅቀዋል፤ ይህ የተጋነነ አይሆንም” ብለዋል።
በአለምአቀፍ የምግብ አቅርቦት ላይም አደጋ ማንዣበቡን የተናገሩት ሲሲ በማዳበሪያ ስርጭት ላይ የሚኖረው መስተጓጎል በዋጋ ላይ ትልቅ ጭማሪ እንደሚያስከትል ጠቅሰዋል። “ሀብታም ሀገራት ይህን ሊቋቋሙት ይችላሉ፤ ነገርግን መካከለኛ ገቢ ባላቸውና ኢኮኖሚያቸው ጠንካራ ባልሆነ ሀገራት መረጋጋት ላይ በጣም፣ በጣም ከባድ ተጽዕኖ ይኖረዋል።”
አሜሪካ ከእስራኤል ጋር በመሆን በኢራን ላይ ጦርነት ማወጇን ተከትሎ የአለምአቀፍ የነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል። የዋጋ ጭማሪው የተከሰተው፣ ኢራን ለተፈጸመባት ጥቃት በሰጠችው አጸፋ በአለም ወሳኝ የሆነውን የነዳጅ መተላለፊያ የሆርሙዝ ወሽመጥን በመዝጋቷ ምክንያት ነው።
አሜሪካ ኢራን ይህን መተላለፊያ እንድትከፍት ብታስጠነቅታትም፤ ኢራን ለመክፈት ፈቃደኛ አልሆነችም።











