Loading...

አርሴናል ከ22 ዓመታት በኋላ የዋንጫ ጥሙን ቆረጠ

አርሴናል ለ22 ዓመታት ሲጠብቅ የነበረውን የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን በማንሳት ጥሙን አርክቷል። ማክሰኞ ምሽት ማንቸስተር ሲቲ ከቦርንማውዝ ጋር 1-1 አቻ ከተለያየ በኋላ  አርሴናል በይፋ የ2025/26 ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮን መሆኑን አረጋግጧል።

በአብዛኛው የውድድር ዘመን የደረጃ ሰንጠረዡን ሲመራ የቆየው የሚኬል አርቴታ ቡድን አሁን ከመጨረሻው ጨዋታ በፊት በ4 ነጥብ ቀዳሚ ሆኗል፤ እሁድ ከክሪስታል ፓላስ ጋር የሚያደርገው ጨዋታም የዋንጫ አከባበር ይሆናል።

አርሴናል ሰኞ በርንሌይን 1-0 ካሸነፈ በኋላ ሲቲ የዋንጫ ተስፋውን ለማቆየት ቦርንማውዝን ማሸነፍ ነበረበት። ኤርሊንግ ሃላንድ በጭማሪ ደቂቃ በቦርንሣውዝ ላይ ያስቆጠራት ጎል ለሲቲ በቂ አልነበረችም።

አርሴናል ባለፉት ሶስት ዓመታት ዋንጫውን በቅርብ ርቀት እያጣ ሁለተኛ ሆኖ ሲጨርስ ብዙ ትችት አስተናግዷል። ነገር ግን ዘንድሮ ቡድኑ በመጨረሻ ጫናውን ተቋቁሞ 14ኛውን የእንግሊዝ ሊግ ዋንጫውን አንስቷል።

አርሴናል በአሰልጣኝ አርሴን ቬንገር እየተመራ ያሸንፈት ውድድሩን በማጠናቀቅ ዋንጫ ካነሳበት ከ2003/2004 ወዲህ ይህ የመጀመሪያው ነው።

የአርሴናል ድል በሰሜን ለንደን ታላቅ የደስታ አከባበር አስከትሏል። ደጋፊዎች በመንገዶች፣ በመጠጥ ቤቶች እና በኤሚሬትስ ስታዲየም አካባቢ ሲዘምሩና ደስታቸውን ሲገልጹ ታይተዋል።

የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የአርሴናል ደጋፊ የሆኑት ኪየር ስታርመርም በኤክስ ገጻቸው “22 ረጅም ዓመታት… ግን በመጨረሻ ወደሚገባን ቦታ ተመልሰናል” ሲሉ ደስታቸውን ገልጸዋል።

የ44 ዓመቱ የአርሰናል ማናጀር አርቴታ ከዓመታት የግንባታ ሂደት በኋላ ክለቡን ወደ ጫፍ መመለስ ችሏል። የቡድኑ ጠንካራ መከላከል፣ ፍጥነት እና የተጫዋቾች አንድነት ለዚህ ስኬት ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።
አሁን አርሴናል የሊግ ዋንጫውን ከማንሳት በተጨማሪ በግንቦት 30 ከፓሪስ ሴንት ዠርማን ጋር በቻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ ይጫወታል፤ ይህንንም ዋንጫ ካሸነፈ ዘንድሮው የአርሴናል ቡድን በክለቡ ታሪክ ከምርጦቹ መካከል ይመዘገባል።

Share this article

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው