ከ1940ዎቹ አጋማሽ እስከ 2001 ድረስ ለግማሽ ምዕተ አመት ያህል በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ጉልህ አስተዋጽኦ ላበረከተው ሰመ ገናና ጽምጻዊ ጥላሁን ገሰሰ ስድስት ኪሎ በሚገኘው የያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት አካባቢ የተሰራው ሀውልት በዛሬው እለት ይፋ ሆኗል።
በሀውልቱ ላይ “ጥላ ከለላዬ ኢትዮጵያ ሀገሬ፣ በጣም ያኮራኛል ከንቺ መፈጠሬ፣
ሰንደቅሽ ከፍ ይበል ይቁም ለዘለዓለም፣
ሰላም ጥጋብ ደስታ ይታይብሽ ባለም” የሚሉ ከዘፈኑ የተወሰዱ የግጥም ሰንኞች ተጽፈዋል።
በተመሳሳይ ከዛሬ ስድስት አመት በፊት ለሞተው ታዋቂ የአፋን ኦሮሞ ድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴስ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ፊት ለፊት ሀውልት እንደቆመለት ኢቢሲ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጠቅሶ ዘግቧል።

ጥላሁን ህይወቱ ያለፈው የዛሬ 17 አመት ነበር። የኢትዮጵያ የሙዚቃ ንጉስ ተደርጎ የሚታየው ጥላሁን ሞት በተለይም በአድናቃዎቹ ዘንድ ከፍተኛ የሀዘን ድባብን ፈጥሮ አልፏል። መንግስትም ድምጻዊው በሙያው ለሀገር አስተዋጽኦ ያደረገ ጀግና ሲል ማሞካሸቱና ብሔራዊ የቀብር ስነስርዓት ማድረጉ የሚታወስ ነው። መንግስት ለአበርክቶው በአዲስ አበባ በቂርቆስ ክፍለከተማ በስሙ አደበባይ ሰይሞለታል።
ከ1950ዎቹ እስከ 1960ዎቹ ድረስ ያሉት አመታት ለጥላሁን ወርቃማ ጊዜያት እንደነበሩ ይነገራል። በድምጹ መስረቅረቅ የተማረኩ አድናቂዎቹም የ“ወርቃማ ጉረሮ” ባለቤት ሲሉ ይጠሩታል። ጥላሁን ኮንሰርት ቢያዘጋጅ ህዝብ ተጋፍቶ የሚሰማው፣ መልእክት ቢያስተላልፍ ተጽዕኖ የሚፈጥር፣ ሙዚቃው በሬዲዮና በቴሌቪዥን ቢከፈት የሚመስጥ በመሆኑ ከዘመን ተጋሪዎቹ በልጦ ኮከብ ድምጻዊ መሆን እንደቻለ ብዙዎች ይስማሙበታል።
ጥላሁን ስለፍቅር፣ ስለሀገርና ስለማህበራዊ ጉዳዮች የሚያወሱ ከ400 በላይ ዘፈኖችን እንደዘፈነ መረጃዎች ያሳያሉ። ከእነዚህ ውስጥ ስለሀገር የዘፈናቸው “እናት ሀገር ኢትዮጵያ”፤ “የሀገሬ ሽታ”፣ “የጠላሽ ይጠላ” እንዲሁም ስለፍቅር የዘፈናቸው “የህይወቴ ህይወት” ፣ “አካል አይንሽን” እና “አልቻልኩም” የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው።
ዛሬ ከተመረቀው ሀውልት ውጭ ለድምጻዊው መታሰበያ የሚሆን ሀውልት የተሰራው ቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ በሚገኘው መካነቃብር ብቻ ነበር። በመንግስት ደረጃ የታሰበው ሀውልት እስካሁን አልተጠናቀቀም።
በ2013 ዓ.ም በስሙ በተሰየመው አደባባይ እምብረት ላይ ግዙፍ የነሀስ ሀውልት ለማስቀመጥ የከተማዋ ባለስልጣናት የመረት ድንጋይ አስቀምጠው የነበረ ቢሆንም እስካሁን አላለቀም።













