ቻይናና ሩሲያ ሀገራት በሆርሙዝ ሰርጥ የሚደረገውን የንግድ መርከቦች እንቅስቃሴ ደህንነት ለማስጠበቅ እንዲተባበሩ የሚያበረታታውን የተመድ የውሳኔ ሀሳብ በኢራን ላይ ያዳላ ነው በማለት ውድቅ አድርገውታል።
በተመድ የአሜሪካ አምባሳደር “ኃላፊነት የሚሰማቸው” ሀገራት አሜሪካ ሰርጡን ለማስከፈት የምታደርገውን ጥረት እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል።
15 አባለት ካሉት የተመድ የጽጥታው ምክርቤት 11ዱ ምክረሀሳቡን ሲደግፉ ሁለቱ ማለትም ሩሲያና ቻይና ተቃውመውታል። ሌሎች ሁለቱ ደግሞ ድምጸ ተአቅቦ ሰጥተዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ትራምፕ “ዛሬ ምሽት የኢራንን ስልጣኔ የሚያጠፉ እርምጃ” እንደሚወስዱ ቢዝቱም፣ ኢራን የሆርሙዝ ሰርጥ እንድትከፍት የተቀመጠውን ቀነ ገደብ ለመቀበል ያሳየችው ምልክት የለም።
እኤአ ፌብሩዋሪ 28፣2026 እስራኤልና አሜሪካ በቅንጅት በኢራን ላይ ጦርነት ከከፈቱ ጀምሮ የነዳጅ ዋጋ እየጨመረ ነው። የዋጋ ጭማሪው ኢራን በአጸፋ በወሰደችው እርምጃ የአለም 1/5 የሚሆነው ነዳጅ መተላለፊያ የሆነውን የሆርሙዝን ሰርጥ በመዝጋቷ ምክንያት የተፈጠረ ነው።
“ረቂቅ የውሳኔ ሀሳቡ ቋሚ የምክርቤት ቤት አባላት የተቃውሞ ድምጽ በመስጠታቸው አልጸደቀም” ሲሉ የባህሬኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብዱላቲፍ ቢን ረሺድ አል ዛይኒ ተናግረዋል።
በተመድ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክ ዋልዝ ሩሲያና ቻይና ኢራን የሆርሙዝ ሰርጥን ለመዝጋት የወሰደችውን እርምጃ በመደገፍ የህክምና እርዳታና ሌሎች አቅርቦቶች እንዳይጓጓዙ አድርገዋል ሲሉ አውግዘዋል።
ነገርግን ሩሲያና ቻይና የቀረበውን ሀሳብ አድሎአዊ ነው በሚል ተቃውመውታል። በተመድ የሩሲያ አምባሳደር ቫሳሊ ነበንዝያ ሩሲያና ቻይና የባህር ላይ እንቅስቃሴ ደህንነትን የሚያስከብር አማራጭ የውሳኔ ሀሳብ ማቅረባቸውን ገልጸዋል። የኢራን የተመድ አምባሳደር አሚር ሰኢድ ኢራቫኒ ሩሲያና ቻይና “የጸጥታው ምክርቤት ወረራን ህጋዊ ለማድረግ ጥቅም እንዳይውል አድርገዋል” በማለት አመስግነዋል።












