ቻይና ኢራን ሉአላዊነቷን ለማስከበር የምታደርገውን ጥረት እንደምትደግፍ ገለጸች

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ቻይና ከኢራን ጋር ላላት የቆየ ግንኙነት ዋጋ እንደምትስጥና ሉአላዊነቷን፣ ደህንነቷን፣ ግዛታዊ አንድነቷንና ክብሯን እንድታስጠብቅ እንደምትደግፋት ማረጋገጣቸውን ዥንዋ ዘግቧል።

የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ የፖለቲካ ቢሮ አባል የሆኑት ዋንግ ይህን የተናገሩት ከኢራኑ አቻቸው አባስ አራቅቺ ጋር የስልክ ውይይት ባደረጉበት ወቅት ነው።

አራቅቺ በቅርብ ጊዜያት ስላለው ቀጣናዊ ሁኔታ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ኢራን እና አሜሪካ ድርድር ላይ ባሉበት ወቅት አሜሪካ በኢራን ላይ ለሁለተኛ ጊዜ ጦርነት መክፈቷን ተናግረዋል።

በውይይቱ መሻሻሎች መኖራቸውን የገለጹት አራቅቺ፣ የአሜሪካ ድርጊት ሁሉንም አለምአቀፍ ህጎችና የኢራንን ቀይ መስመሮች የሚጥስ ነው ብለዋል። ኢራን አማራጭ እንድታጣና በሙሉ ኃይሏ ወደ መከላከል እንድትገባ ሆናለች ብለዋል። ሚኒስትሩ ቻይና ያላትን ሚዛናዊ እና ፍትሃዊ አቋም በይፋ መግለጿን ጠቅሰው በቀጣናው ያለውን ውጥረት ለማርገብ ያላትን አዎንታዊ ሚና አጠናክራ እንደምትቀጥል ተስፋ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ዋንግ ዪ በበኩላቸው ቻይና በወቅታዊው የኢራን ሁኔታ ላይ ያላትን በመርህ ላይ የተመሰረተ አቋም በድጋሚ ያረጋገጡ ሲሆን ኢራን ህጋዊ መብቶቿን እና ጥቅሞቿን ለማስከበር ለምታደርገው ጥረት ድጋፋቸውን ገልጸዋል። ዋንግ ዪ አክለው እንዳሉት ቻይና፣ አሜሪካና እስራኤል በኢራን ላይ የሚያደርጉትን ዘመቻ እንዲያቆሙ፣ ውጥረቱ እንዳይባባስና ግጭቱ ወደቀጠናው እንዳይስፋፋ እንዲከላከሉ አሳስባለች።

ዋንግ ኢራን በከባድ እና ውስብስብ ወቅታዊ ሁኔታ ውስጥ ብትሆንም፣ ብሔራዊና ማህበራዊ መረጋጋቷን እንደምታስቀጥል ጎረቤቶቿ ለሚያነሱት ምክንያታዊ ስጋት ትኩረት እንደምታደርግና የቻይና ዜጎችን ደህንነት እንደምትጠብቅ እምነት አላቸው።
አራቅቺም ኢራን የቻይና ዜጎችንና ተቋማትን ደህንነት ለመጠበቅ የሚቻላትን ሁሉ እንደምታደርግ አረጋግጠውላቸዋል።

ዘገባው የCGTN ነው

Share this article

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው