Loading...

የአፍሪካ ሀገራትን ተጠቃሚ የሚያደርገውና በቅርቡ ተግባራዊ የሚሆነው የቻይና ዜሮ  ታሪፍ ፖሊሲ

የቻይና መንግስት በቅርቡ ባጸደቀው የአምስት አመት የልማት እቅድ ውስጥ የዜሮ ታሪፍ (Zero tariff) ፖሊሲን አስተዋውቋል። እ.ኤ.አ. ከግንቦት 1፣ 2026 ጀምሮ ተግባራዊ በሚሆነው በዚህ የገበያ እድል ከቻይና ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው 53 የአፍሪካ ሀገራት ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሏል።

ቻይና ይህን መርሃግብር ያስተዋወቀችው፣ አሜሪካ ቀደም ሲል ምርቶቻቸውን ወደ አሜሪካ ገበያ ከቀረጥ ነጻ የሚያቀርቡ በርካታ የአፍሪካ ሀገራትን ከቀረጥ ነጻ እድል (African Growth and Opportunity Act/AGOA) ካገደችና ከሰረዘች በኋላ ነው። እስከ 2025 ድረስ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሃራ በታች ያሉ 17 ሀገራት ከአጎኦ ውጭ ሆነዋል። 32 የሚሆኑ ሀገራት የገበያ እድሉ ተጠቃሚ ሆነው የቀጠሉ ሲሆን ሌሎች ደግሞ የሰብዓዊ መብት ጥሰትንና መፈንቅለ መንግስትን በመሳሰሉ ምክንያቶች የመታገድ ወይም የመሰረዝ እጣፈንታ ደርሶባቸዋል።

ቻይና “የክፉ ቀን ጓደኛ”

ከአጎአ ጋር የሚመሳሰለው የቻይና የዜሮ ታሪፍ የገበያ እድል በተለይም ከአሜሪካው አጎአ ለተሰረዙት ሀገረት በጣም ወሳኝ ነው። አሜሪካ ሀገራትን ከመርሃግብሯ እያስወጣች ባለችበት ወቀት፣ ቻይና አስተማማኝ ገበያ ለሚፈልጉ የአፍሪካ ሀገራት “የክፉ ቀን ጓደኛ” ሆና ብቅ ብላለች። በዚህ የዜሮ ታሪፍ መርሃግብር የአፍሪካ ሀገራት የግብርና ምርቶቻቸውን ወደ ሰፊው የቻይና ገበያ ያቀርባሉ።

ኢትዮጵያ ከዚህ የዜሮ ታሪፍ ገበያ ተጠቃሚ ለመሆን አልማለች። ከመጋቢት 16-17 በአዲስ አበባ በተካሄደው የሆርቲካልቸር ኤግዚቢሽን ላይ  የኢትዮጵያ አምራቾች አበባ፣ ፍራፍሬና አትክልት ወደ ቻይና ለመላክ ያላቸውን ፍላጎት አሳይተዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ወንድአለ ሀብታሙ ለአፍሮኢንሳይት እንደገለፁት ኢትዮጵያ በተለይ የግብርና ምርቶችን በመላክ የቻይናን የዜሮ ታሪፍ ገበያ እድልን ለመጠቀም ፍላጎት አላት። ምክትል ዳይሬክተሩ የግብርና ምርትን ማሳደግ የተፈጠረውን የገበያ እድል ሙሉ ለሙሉ ለመጠቀም የሚያሰችል ነው ብለዋል።

“ለምሳሌ በዚህ አመት(2026) ከፍተኛ መጠን ያለው የሆርቲካልቸር ምረት ወደ ቻይና ገበያ ለመላክ የሚያስችል ስምምነት ከቻይና ጋር ተፈራርመናል። ይህን ገበያ ከሚጠቀሙት የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ ኢትዮጵያ አንዷ ትሆናለች። ለዚህ ዝግጁ ነን።”

የቻይና ገበያ “ግዙፍ” እና “ጠንካራ” ነው ያሉት  ዶክተር ወንዳለ የገበያ እድሉን ማግኘት አስፈላጊነት በአጽንኦት ተናግረዋል
“የቻይናን ገበያ ስንናስብ መጀመሪያ ሰፊ ነው። ሁለተኛ ትርፉም ትልቅ ነው። በዚህ ምክንያት የኢትዮጵያ መንግስትና የሆርቲካልቸር ዘርፉ ከቻይና ገበያ የሚቻለውን ያህል ትርፍ ያገኛል።”

የሲዲማ ክልል የአምራቾች ማህበር ስራ አስኪያጅ የሆነው አዳነ አሜሎ ለአፍሮ ኢንሳይት እንደተናገረው የቻይና ዜሮ ታሪፍ “አርሶ አደሮቻችን ትርጉም ባለው መልኩ የሚጠቅምና አጠቃላይ ኢኮሚኖሚውን የሚያጠናክር ነው።”

አፍሪካ 120 ቢሊየን ዶላር ዋጋ ያለው ምርት ወደ ቻይና ገበያ እየላከች ነው። ይህ አሀዝ አሁን በተዋወቀው የዜሮ ታሪፍ ፖሊሲ ምክንያት ከፍ እንደሚል ይገመታል። ፖሊሲው የንግድ ልውውጥ መጠንን ከመጨመር ባለፈ፣ የቻይናና አፍሪካ የኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ወዳጅነት ወደ ከፍተኛ ደረጃ ያደርሰዋል ተብሏል

Share this article

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው