በሲሊኮን ቫሊ ታሪክ ከፍተኛ ትኩረት ስቦ የሰነበተውና በዓለማችን ቁንጮ ቢሊየነር ኢሎን መስክ እንዲሁም በኤአይ (AI) ንጉሡ ሳም አልትማን መካከል ሲካሄድ የነበረው የፍርድ ቤት ፍልሚያ አስገራሚ ፍጻሜ አግኝቷል። በአሜሪካ ኦክላንድ ፌደራል ፍርድ ቤት የተሰየመው ባለ 9 አባላት የዳኞች ቡድን (Jury) የኢሎን መስክን ክስ ሙሉ በሙሉ ውድቅ በማድረግ ለኦፕንኤአይ እና ለሳም አልትማን ወግኗል።
የዳኞች ቡድን ለሁለት ሰዓታት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በሰጠው ወሳኝና አስገራሚ ውሳኔ ኢሎን መስክ ክሱን ያቀረበው “ሕጋዊ የጊዜ ገደቡ ካለፈ በኋላ ነው” (Too Late) በሚል መዝገቡን ዘግቶታል።
“የበጎ አድራጎት ድርጅትን መስረቅ”፦ የ38 ሚሊዮን ዶላር ክርክር
ኢሎን መስክ እ.ኤ.አ በ2024 በከፈተው በዚህ ክስ ኦፕንኤአይ መጀመሪያ ሲመሰረት ለሰው ልጅ ጥቅም የሚሰራ “ለትርፍ ያልቆመ ድርጅት” (Nonprofit) ሆኖ ሳለ፣ ሳም አልትማንና ግሬግ ብሮክማን ማይክሮሶፍትን ጨምሮ ከግዙፍ ባለሀብቶች ቢሊዮኖችን በመቀበል ወደ ትርፍ አሳዳጅነት ቀይረውታል ሲል ተከራክሯል። የመስክ ጠበቆች ድርጊቱን “የበጎ አድራጎት ድርጅትን እንደ መስረቅ ነው” በማለት ቢገልጹትም፣ ፍርድ ቤቱ ግን አልተቀበለውም።
ኦፕንኤአይ በበኩሉ መስክ ራሱ ድርጅቱን ወደ ትርፍ ፈላጊነት ቀይሮ ከራሱ የቴስላ ኩባንያ ጋር ለመቀላቀል ፈልጎ እንደነበርና ፍላጎቱ ሳይሳካ ሲቀር ድርጅቱን ጥሎ መውጣቱን የሚያሳዩ መረጃዎችን አቅርቧል። ድርጅቱ ወደ ትርፍ ፈላጊነት መዋቀሩን መስክ ገና በ2017 እያወቀ፣ ክሱን አሁን ማቅረቡ በሕግ የተቀመጠውን የ3 ዓመት የጊዜ ገደብ (Statute of Limitations) የሚጥስ ነው ሲል ተከራክሮ አሸንፏል።

ለ11 ቀናት በዘለቀው የፍርድ ቤት ውሎ የሁለቱ መሪዎች ታማኝነት እና ስብዕና በከፍተኛ ሁኔታ ተፈትኗል፦
የመስክ ጠበቆች ሳም አልትማንን (OpenAI CEO) “ውሸታም እና አታላይ” በማለት የገለጹት ሲሆን የቀድሞ የኦፕንኤአይ ከፍተኛ ሰራተኞች (የቀድሞዋን የቴክኖሎጂ ኃላፊ ሚራ ሙራቲን ጨምሮ) አልትማን “ለአንዱ አንድ ነገር ተናግሮ ለሌላው ተቃራኒውን የሚናገር ሰው ነው” ማለታቸውን አስታውሰዋል። አልትማን በፍርድ ቤት “እኔ ታማኝ ሰው ነኝ ብዬ አምናለሁ” በማለት ተከላክሏል።
ኢሎን መስክ (Elon Musk) በፍርድ ቤት ቀርቦ በነበረበት ወቅት ለቀረቡለት ጥያቄዎች ጠንከር ያሉና ስሜታዊ ምላሾችን ሲሰጥ የነበረ ሲሆን ጠበቆቹ እሱ ራሱ 100% ታማኝ መሆኑን በፍርድ ቤት ማረጋገጥ አልቻሉም።

ይህ ውሳኔ ለሳም አልትማን እና ለኦፕንኤአይ ትልቅ እፎይታ የሰጠ ነው። ድርጅቱ በያዝነው የ2026 ዓመት መጨረሻ ላይ በ1 ትሪሊዮን ዶላር ግምት ወደ አክሲዮን ገበያ (IPO) ለመግባት ላቀደው ታላቅ የንግድ ጉዞ አረንጓዴ መብራት ሆኖለታል።
የፌደራሉ ዳኛ ይቮን ጎንዛሌዝ ሮጀርስ (Yvonne Gonzalez Rogers) የዳኞቹን ውሳኔ በማጽደቅ፣ የመስክ ጠበቆች ይግባኝ ለማለት ቢሞክሩ እንኳ ውሳኔውን “በቦታው ላይ ውድቅ እንደሚያደርጉት” በግልጽ ተናግረዋል።










