በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሚመራው የአሜሪካ አስተዳደር “ራሷን [ከምዕራቡ አለም] ካገለለችውና” በቀይ ባህር ጠረፍ ላይ ወሳኝ ቁጥጥር ካላት ኤርትራ ጋር ግንኙነቷን እንደገና ለመጀመር ንግግር እያደረገች እንደምትገኝ ተዘግቧል።
አሜሪካ ይህን ለማድረግ የወሰነችው ጦር የተማዘዘቻት ኢራን በቀይ ባህር ቀጣና ወሳኝ የንግድ እንቅስቃሴ መስመር የሆነውን የባብ ኤል ማንዴብ ሰርጥን ለመዝጋት እየዛተች ባለችበት ወቅት ነው።
ዎልስትሪት ጆርናል የተባለው የአሜሪካ ጋዜጣ የቀድሞና የአሁን ከፍተኛ የአሜሪካ ባለስልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ አሜሪካ ከኤርትራ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማስተካከል በበርካታ አስርት አመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጣለባትን የተወሰኑ ማዕቀቦች ለማንሳት እያሰበች ነው። ይህ ፕሬዝዳንት ትራምፕ የሁለቱን ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለማድረስ እያደረጉ ያሉት ጥረት አካል ነው ተብሏል።
ከኤርትራ ጋር ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማደስና በሀገሪቱ ላይ ተጥለው የነበሩ ማዕቀቦችን ለማንሳት ግምገማ እየተደረገ መሆኑንና አለመጠናቀቁን ዘገባው ጠቅሷል። እንደዘገባው ይህን አቅድ የሚመሩትና ከኤርትራ ባለስልጣናት ጋር እየተነጋገሩ ያሉት የአሜሪካ መልእክተኛ ማሳድ ቦውለስ ናቸው።
አሜሪካ ግንኙነቱን ለማደስ የፈለገችው በመካከለኛው ምስራቅ ከአጋሯ እስራኤል ጋር በመቀናጀት የጀመረችው ጦርነት የባህር ደህንነት ላይ ስጋት በመደቀኑ ምክንያት ነው። አሜሪካ 700 ኪሎሜትር የሚረዝም የቀይ የባህር ጠረፍ ካለት ኤርትራ ጋር በመወዳጀት በቀይ ባህር ላይ የሚካሄደውን ወሳኝ የንግድ እንቀስቃሴ ሊያስተጓጉሉ የሚችሉትን ኢራንና አጋሮቿን በተለይም የየመን የሀውቲ ታጣቂዎችን ለመግታት እንደሚረዳት ተገልጿል።
ለአሜሪካ ጥቃት አጸፋ የአለም 20 በመቶ ነዳጅ የሚተላለፍበትን የሆርሙዝ ሰርጥ የዘጋችው ኢራን የቀይ ባህር መተላለፊያን እንደመትዘጋ ዝታለች። በኢራንና አሜሪካ መካከል ያለው ተኩስ አቁም በአሜሪካ በኩል የተራዘመ ቢሆንም፣ በተኩስ አቁም የተካተቱት ነጥቦች ተግባራዊ ባለመሆናቸው ጦርነቱ ድጋሚ ሊቀሰቀስ የሚችልበት እድል ሰፊ ነው።













