የኢትዮጵያን ቡና ለማስተዋወቅና የኢትዮ-ቻይናን ወዳጅነት ለማክበር ያለመ ስብሰባ በቻይና ተዘጋጀ

የኢትዮጵያ ቡና አይነቶችን ገበያ ተደራሽነት ለማስፋት ያለመ ስብሰባ በቻይና ሁናን ግዛት ከዛሬ ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል።

በስብሰባው መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ታየ አጽቀስላሴ ስብሰባው የተዘጋጀው ስለቡና ብቻ ለመወያየት ሳይሆን ለረጅም ጊዜ የቆየውንም የኢትዮጵያና ቻይና ወዳጅነት ለማክበር ጭምር ነው ብለዋል።

“ይህ ስብሰባ አሁን ከፍተኛ የሁልጊዜ ስትራቴጂካዊ ወዳጅነት ላይ የደረሰው በኢትዮጵያና ቻይና መካከል ያለው ቀና የትብብር መንፈስ ማሳያ ነው” ሲሉ ተናግረዋል ፕሬዝዳንቱ።

ፕሬዝደንቱ እንደገለጹት በአፍሪካ-ቻይና ትብብር ማዕቀፍ መሰረት ኢትዮጵያ ግብርናን፣ የአረንጓዴ ልማትን፣ ንግድና ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንትን የኢንዱስትሪ ለውጥ ለማምጣት የመጠቀም ራዕይ አላት። እንደ ፕሬዝደንቱ ከሆነ ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ከግብርና በተጨማሪ በወሳኝ ማዕድናትና እሴት በሚጨምሩ እቃዎች ዙሪያ በትብብር መስራት ትፈልጋለች።

የቡና ዘርፉ 25 በመቶ የሚሆነውን የስራ እድልና 30 በመቶ የሚሆነውን የውጭ ንግድ ገቢ እንደሚሸፍን ፕሬዝዳንቱ ጠቅሰዋል።

በዚህ ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያ ልኡክ ቡድንና የዦዡ ከተማ ከንቲባን ጨምሮ የቻይና ባለስልጣናት በቦታው መገኘታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

እንደዘገባው በኢትዮጵያ በኩል፣ በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበውን ጨምሮ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ ከፍተኛ ባለስልጣናት ተገኝተዋል።

ቻይና የኢትዮጵያ ቡና በመግዛት ከአምስት አመታት በፊት ከነበረችበት 33ኛ ደረጃ በዚህ አመት 4ኛ ደረጃ ይዛለች። ባለፈው አመት ኢትዮጵያ 35ሺ ቶን ቡና ወደ ቻይና መላክ ችላለች።

Share this article

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው