የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ በኢራኑ ጦርነት ምክንያት የሆርሙዝ ሰርጥ በመዘጋቱ 120ሺ ሜትሪክ ቶን ነጭ ናፍጣና 60ሺ ሜትሪክ ቶን የአውሮፕላን ናፍጣ የጫኑ ሶስት መርከቦች በአረብ ባህረሰላጤ መቆማቸውን አስታውቋል።
ሚኒስቴሩ እንደገለጸው በሰርጡ መዘጋት ምክንያት ሳኡዲ አረቢያ፣ ኩየት፣ አረብ ኢምሬትስ እና ኢራቅ የመሳሰሉ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በቀን ወደ ገበያ ያወጡት የነበረው 140 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ተቋርጧል።
ኢትዮጵያ 60 በመቶ ነጭ ናፍጣና 100 በመቶ የአውሮፕላን ነዳጅ ከኩየት መንግስትና ቀሪውን 40 በመቶ ነጭ ናፍጣ እንዲሁም 100 በመቶ ቤንዚንና ጥቁር ናፍጣዎችን በአለምአቀፍ ጨረታ እንደምትገዛ መግለጫው ጠቅሷል።
ነገርግን የኩየቱ አቅርቦት በመዘጋቱና መንግስት በጨረታ ወደ አጣዳፊ ግዥ በመግባቱ የአውሮፕላን ነዳጅን በ86.33 ዶላርና ነጭ ናፍጣን በ92.88 ዶላር በበርሜል በሆነ ወድ ዋጋ እየገዛ ነው ብሏል መግለጫው።
መንግስት “መደበኛ አቅርበት እንዳይቋረጥ ከተባራሪ ገበያ (spot market)” በውድ ዋጋ እየገዛ በመሆኑ አዲስ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ አስገዳጅ ነው ብሏል።
መንግስት በአንድ ወር ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ በትናንትናው እለት(መጋቢት 23፣ 2018) ይፋ ባደረገው አዲስ ዋጋ በሊትር እስከ 27 ብር ጭማሪ አሳይቷል።
ባለፈው ሳምንት 139 ብር ሲሸጥ የነበረው ነጭ ናፍጣ አሁን ላይ 24 ብር ጨምሮ 163.09 ብር እየተሸጠ ሲሆን 132.18 ብር ሲሸጥ የነበረው ቤንዚን 10 ብር ጨምሮ 142.21 ደርሷል።
ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች የነዳጅ ምርቶች ማለትም ኬሮሲን 151.39፣ ቀላል ጥቁር ናፍጣ 163.98 ብር፣ ከባድ ጥቁር ናፍጣ 160.68 ብር እንዲሁም የአውሮፕላን ነዳጅ 150.48 ብር እየተሸጡ ናቸው።
መንግስት ለነዳጅ የሚያደርገው ድጎማ ከ272 ቢሊዮን ብር በላይ ማለፉን የገለጸው መግለጫው የአቅርቦት እጥረትና የዋጋ ጭማሪ ቀውሱ እስከሚስተካከል ስርጭቱን የሚከታተል ቡድን ተቋቁሟል ብሏል። ነዳጅን በቁጠባ መጠቀም እንደሚገባ ያሳሰበው መንግስት ቅድሚያ ነዳጅ የሚሰጣቸውን ተሽከርካሪ አይነቶችን ዝርዝር ይፋ አድርጓል።
ኢራን አንድ አምስተኛ የሚሆነው የአለም የነዳጅ አቅርቦት የሚተላለፍበትን የሆርሙዝ ሰርጥ በመዝጋቷ ምክንያት አለምአቀፍ የነዳጅ ግብይት በከፍተኛ ሁኔታ ተስተጓጉሏል።













