ዕዳዋን መክፈል የምትችልበትን ሁኔታ ለመፍጠር እየተደራደረችና ኢኮኖሚዋን ለማረጋጋት እየጣረች ያለችው ኢትዮጵያ መገበያያ ገንዘብ ብር ከአርጀንቲና ፔሶና ከቱርክ ሊራ ቀጥሎ ሶስተኛው ደካማ ገንዘብ መሆኑን ብሉምበርግ ዘግቧል።
እ.ኤ.አ. በ2025 የብር ዋጋ ከዶላር አንጻር 15 በመቶ መቀነሱንና ይህም የዶላር እጥረት ጫናን፣ የዋጋ ውድነት ጫናንና የኢንቨተሮችን ስጋት እንደሚያሳይ ዘገባው ጠቅሷል።
እንደዘገባው ከሆነ የብር አቅም ከኢትዮጵያ ብድር የመክፈል አቅም መሻሻል ጋር የተያያዘ ነው።
ኢትዮጵያ ብድር ለመክፈል እያደረገች ያለውን ድርድር (debt restructuring ) በቡድን 20 ሀገራት ማዕቀፍ እ.ኤ.አ. በ2026 አጋማሽ ለማጠናቀቅ እቅድ ይዛለች። መንግስት የ3.5 ቢሊየን ዶላር እዳ በመክፈል(restructure) በማድረግ ዙሪያ ከቻይናና ፈረንሳይ ጨምሮ ከኦፊሻል ክሬዲተሮች አባለት ወይም አበዳሪዎች ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል።
ነገርግን ከግለሰብ አበዳሪሪዎች ጋር ያለው ድርድር አልተቋጨም። የኢትዮጵያን አንድ ቢሊዮን ዶላር ዩሮቦንድ ከያዙ ግለሰብ አበዳሪዎች ጋር የተደረገው ድርድር እ.ኤ.አ በ2023 ያለስምምነት መጠናቀቁ ይታወሳል።
ባለፈው አመት ሰኔ ወር ኢትዮጵያ ከአይኤምኤፍ የ3.4 ቢሊዮን ዶላር ብድር አግኝታ ነበር። በ2025 መጨረሻ ሰባተኛዋ የአይኤምኤፍ ግዙፍ ተበዳሪ ሀገር ሆናለች። መንግስት ይህን ብድር ያገኘው የምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲመራ ካደረገ፣ የፋይናንስ ዘርፉ ለውጭ ክፍት እንዲሆን ከወሰነና የመንግስት ድርጅቶችን ወደ ግል ለማዛወር የሚያስችለውን እቅድ ካቀረበ በኋላ ነው። አይኤምኤፍ በዚህ ወር መጀመሪያ በስራ አሰፈጻሚ ቦርድ ባይጸድቅም ለኢትዮጵያ 261 ሚሊዮን ዶላር እንዲለቀቅላት ፈቅዷል።
አይኤምኤፍ በተወሰኑ ቁልፍ ዘርፎች የኢኮኖሚ መሻሻል መኖሩን ጠቅሷል። የውጭ ንግድ መሻሻሉን፣ የመንግስት ገቢ መጨመሩንና አመታዊ የዋጋ ግሽበት የምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲወሰን ከተደረገ ከጥቂት ቆይታ በኋላ ከነበረው 18.6 በመቶ ወደ 10.9በመቶ መቀነሱን አይኤምኤፍ በጥንካሬ የጠቀሳቸው ናቸው።
ነገርግን ኢትዮጵያ አሁንም የዶላር እጥረት እንዳለበትና በህጋዊና በጥቁር ገበያ የምንዛሬ ተመን መካከል ያለው ክፍተት ሰፊ እንደሆነ ዘገባው ያመለክታል።













