በጋና በየሳምንቱ ረቡዕ መንገድ ላይ ሲወጡ አንድ ለየት ያለ ነገር ያስተውላሉ፤ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ተማሪዎች፣ ነጋዴዎች አልፎ ተርፎም የውጭ ሀገር ዲፕሎማቶች በባህላዊውና ውብ በሆነው የ”ፉጉ” (Fugu) ልብስ ተውበው ይታያሉ።
ይህ የሆነው የጋና መንግስት በየሳምንቱ ረቡዕ “የፉጉ ቀን” (Fugu Day) ተብሎ እንዲከበር ባስተላለፈው ጥሪ መሠረት ነው። ዓላማውም የሀገሪቱን የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ማነቃቃትና የጋናውያንን የማንነት ኩራት ለዓለም ማሳየት ነው።

“ፉጉ” ምንድን ነው? ፉጉ (በአንዳንድ አካባቢዎች ‘ስማክ’ ተብሎ የሚጠራው) ከሰሜን ጋና የመነጨ ከጥጥ በእጅ ተፈትሎና ተሸምኖ የሚሰራ፣ በተለይ ለወንዶች ግርማ ሞገስን የሚሰጥ ልብስ ነው። ልብሱ ከታች ሰፋ የሚል በመሆኑ ሲራመዱበት ወይም ሲጨፍሩበት የሚፈጥረው ወዘና ለማየት እጅግ ማራኪ ነው።
ለምን ረቡዕ ተመረጠ? ጋናውያን “ረቡዕ”ን እንደ ስራ ቀን ብቻ ሳይሆን አጋማሽ ሳምንት ላይ ደርሰን የሳምንቱን ድካም በባህላዊ ውበት የምናድስበት ቀን ነው ይላሉ።
ዘንድሮ ደግሞ ነገሩ ከፋሽን አልፎ ለኢኮኖሚው ትልቅ ትርጉም አለው። ብዙ ወጣቶች በፉጉ ሽመናና ስፌት ላይ ተሰማርተው ስራ እንዲያገኙ መንገድ ከፍቷል።

በአክራ ዋና ዋና መንገዶች ላይ የሚታየው ትዕይንት ለየት ያለ ነው።
“ቀደም ሲል ፉጉ የምንለብሰው ለሰርግ ወይም ለትላልቅ በዓላት ብቻ ነበር” ይላል አንድ የአክራ ነዋሪ በሳቅ ታጅቦ። “አሁን ግን ረቡዕን በጉጉት እንጠብቃለን። ልብሱ ሰፋ ያለ ስለሆነ ለአየሩም ምቹ ነው፤ ሆድ ቢወጣም አይታወቅም!” በማለት የልብሱን ጠቀሜታ በጨዋታ መልክ ይገልጻል።
የጋና ቱሪዝም ባለስልጣን ይህንን ቀን ተከትሎ “Fugu Challenge” በሚል በማህበራዊ ሚዲያ ውድድር ያዘጋጀ ሲሆን ምርጥ አለባበስ ያላቸው ጋናውያን ልዩ ሽልማት እንደሚጠብቃቸውም አስታውቋል።











