በጋምቤላው ግጭት የተጎዱ ሰዎች ቁጥር መጨመሩንና የጤና ተቋማትን መደበኛ ስራ መስተጓጎሉን ኤምኤስኤፍ ገለጸ

በኢትዮጵያ ጋምቤላ ክልል ለሳምንታት እየተካሄደ ያለው ግጭት የክልሉ መንግስት አስቸኳይ የሰአት እላፊ ገደብ ኢንዲጥል አስገድዶታል።

የብሔር መልክ ያለው እንደሆነ የሚነገርለት ይህ ግጭት የበርካታ ሰዎችን ጉዳትና ሞት አስከትሏል።

አለምአቀፉ ግብረሰናይ ድርጅት ድንበር የለሽ የዶክሮች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) ትናንት ባወጣው መግለጫ በጋምቤላ ክልል ያሉ የጤና ተቋማት በቁስለኞች መጨናነቃቸውንና በዚህ ምክንያት መደበኛ የጤና አገልግሎት ስራዎች መስተጓጎላቸውን ገልጿል።

ኤምኤስኤፍ እየተባባሰ በመጣው ግጭት በትናትናው እለት ብቻ 100 የተጎዱ ሰዎች መቀበሉንና ቁጥሩ ሊጨምር እንደሚችል ጠቅሷል።

እንደመግለጫው ከሆነ ኤምኤስኤፍ የችግሩን ስፋት ከግምት በማስገባት ለብዙዎች ምላሽ የሚሰጥ ስርአት ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ በመዘርጋት እስካሁን 15ዐ ተጎጅዎችን መቀበል ችሏል።

ተመላላሽና ሪፈር የሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች አገልግሎት እያገኙ አለመሆናቸውን የጠቀሰው ኤምኤስኤፍ ግጭቱ በጤናው ዘርፍ ያሳደረው ተጽዕኖ ያሳስበኛል ብሏል።

ይህ ግጭት በደቡብ ሱዳን የነበረውን የእርስ በእርስ ጦርነት ሸሽተው በክልሉ የተጠለሉ ስደተኞችንም ስጋት ውስጥ የከተተ ነው ተብሏል።

የክልሉ መንግስት ከምሽቱ 2:00 እስከ ጠዋቱ 12 :00 ድረስ የሚቆይ የእንቅስቃሴ ገደብ ጥላል፤ ፍቃድ የሌለው ማንኛውም ሰው የጦር መሳሪያ እንዳይዝ ከልክሏል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እንገደጸው ግጭቱ ከተስተዋለባቸው ቦታዎች መካከል ጋምቤላ ከተማ፣ ኢታንግ ልዩ ወረዳና አቦል አካበቢ ይገኙበታል።
የኢትዮጵያ መንግስት ግጭቱን ለመቆጣጠር ወደ ቦታው ኃይል መላኩ ተሰምቷል። ነገርግን ግጭቱ እንዴት እንደተነሳና የሰዎች ሞትና ጉዳት እንዳደረሰ ግልጽ አላደረገም።

Share this article

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው