Loading...

በጋሞ ዞን ከባድ ዝናብ ባስከተለው የመሬት መንሸራተት አደጋ የሞቱ ሰዎች 70 ደረሰ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በተፈጠረው የመሬት መንሸራተት በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች ሲሞቱ በሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን ክልሉ አስታውቋል።

የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ የቢሮ ኃላፊውን ኃይለማርያም ተስፋዬን ጠቅሶ እንደዘገበው እስካሁን በአደጋው ህይወታቸው ያጡ ሰዎች ቁጥር 70 ደርሷል

መጋቢት 1፣2018 ዓ.ም የጣለው ከባድ ዝናብ በዞኑ አራት ወረዳዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን የገለጹት ኃላፊው ይህን ሪፖርት ይፋ እስካደረጉበት እስከ ከቀኑ 8:00 ድረስ 190 የመኖሪያ ቤቶች መውደማቸውንና 3480 ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን ጠቅሰዋል። ዝናቡ ከመሬት መንሸራተት በተጨማሪ ጎርፍ አስከትሎ በንብረት ላይም ጉዳት ማድረሱን ኃላፊው ገልጸዋል።

በቀጣዮቹ 10 ቀናት ዝናቡ እንደሚቀጥል የትንበያ መረጃ መኖሩን የገለጹት ኃይለማርያም መንግስት በአሁን ሰአት ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች ምግብ፣ ምግብ ነክ ያልሆኑና የጤና ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል።

በ2016 ዓ.ም. በእዚሁ ክልል ውስጥ ጎፋ ዞን በተከሰተው ከባድ የመሬት መንሸራተት አደጋ ከ200  በላይ ሰዎች ህይወታቸው ማጣታቸው ይታወሳል

የጋሞ ዞን ለመሬት መንሸራተት አደጋ ለምን ተጋላጭ ሆነ?

በጋሞ ዞን አሁንም ከባድ ዝናብ ሊቀጥል እንደሚችልና አደጋውም ሊሰፋ እንደሚችል የአየር ንብረት መረጃዎች ያመለክታሉ።

የዞኑ ተፈጥሯዊ አቀማመጥ(Topography) ፣ ከባድ ዝናብ፣ የአፈር አይነት፣ የደን መጨፍጨፍና የአየር ንብረት ለውጥ በዞኑ ብሎም በክልሉ ለሚከሰቱ ተደጋጋሚ የመሬት መንሸራተት አደጋዎች ዋና ዋና ምክንያቶች እንደሆኑ ይጠቀሳሉ። አካባቢዎቹ ገደለማና ተደፋት ያሉባቸው በመሆናቸው ለናዳና ለመሬት መንሸራት የበለጠ ተጋላጭ ያደርጋቸዋል።

ከባድና ተከታታይነት ያለው ዝናብ በሚጥልበት ጊዜ መሬቱ ከፍተኛ ውሃ እንዲይዝ(Saturate) ስለሚያደርገው መሬቱ ጥንካሬውን እንዲያጣና በቀላሉ እንዲናድ ያደርገዋል። በ2016 በክልሉ በጎፋ ዞን የተከሰተው ከባድ አደጋ ምክንያት የሁለት ተከታታይ ቀናት የጣለው ከባድ ዝናብ ነበር።

በአካባቢው ያለው የአፈር አይነትም ለአደጋው መከሰት የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው ይገለጻል። የአካባቢው አፈር ሸክላማ ስለሆነ ውሃን የመያዝ ባህሪ ስላለው፣ ውሃ ከያዝ በኋላ ስለሚከብድ የመንሸራተት እድሉን ይጨምረዋል።
የደን መጨፍጨፍና የመሬት አጠቃቀም ጉድለትም እንዲሁ የአደገውን መከሰት እድል ይጨምራሉ። በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚከሰቱ ያልተለመዱና ድንገተኛ የሆኑ ከባድ ዝናቦች መብዛታቸው ለአደጋው መደጋገም ተጨማሪ ምክንያት መሆናቸውም ተዘግቧል።

Share this article

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው