ኢራንና አሜሪካ በኦማን ወሳኝ ንግግር ጀመሩ

ኢራን እና አሜሪካ በመካከላቸው ያሉትን ጉልህ ልዩነቶች ለመፍታት ከፍተኛ ግምት የተሰጠውን ንግግር በዛሬው እለት በኦማን መጀመራቸው ተዘግቧል። በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ልዩነት የሚሰፋና ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች የሚከሽፉ ከሆነ በመካከለኛው ምስራቅ ሌላ ጦርነት ሊነሳ ይችላል የሚል ስጋት ተፈጥሯል።

ሁለቱም ወገኖች በኢራን የኑክሌር መርሃግብር ውዝግብ ጉዳይ ለመነጋገር ያላቸውን ፍላጎት ቢያሳዩም ዋሽንግተን ንግግሩ የኢራንን ባለስቲክ ሚሳይሎች በቀጣናው ያሉ ተመጣቂዎችን መርዳት ጉዳይና የራሷን ህዝብ የያዘችበት መንገድ የድርድር ነጥቦች እንዲሆኑ እንደምትፈልግ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ባለፈው ረብዕ ተናግረዋል።

አራን በበኩሏ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራቅቺና የአሜሪካ የመካከለኛው ምስራቅ መልእክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ በኑክሌር ጉዳይ ብቻ እንዲመክሩ እንደምትፈልግ እየገለጸች ነው። በጋዛ ተኩስ አቁም ንግግር ወቅት ሚና የነበረው የፕሬዝዳንት ትራምፕ አማች ጃረድ ኩሽነር በንግግሩ ይሳተፋል ተብሏል።

“ኢራን ወደ ንግግሩ የገባቸው የባለፈውን እያስታወሰች ነው። በቅን ልቦናና መብታችንን አስጠብቀን እንነጋገራለን” ሲሉ አራቅቺ በኤክስ ገጻቸው አስፍረዋል።

የኢራን አመራር አሜሪካ በኢራን አቅራቢያ የጦር መሳሪያ ካከማቸች በኋላ ፕሬዝደንት ትራምፕ ኢራንን ሊያጠቁ ይችላሉ የሚል ስጋት ውስጥ ገብቷል። አሜሪካ እስራኤል የ12 ቀናት ጥቃት በኢራን ላይ በሰነዘረችበት ወቅት በመጨረሻዎቹ ቀናት የኢራንን የኑክሌር ይዞታዎች መምታቷ ይታወሳል። ቴህራን ከእዚያን ጊዜ ጀምሮ ኑክሌር የማበልጸግ ስራዋን እንዳቆመች እየገለጸች ነው።

አሜሪካ በኢራን ዙሪያ ግዙፍ የሆነ የባህር ኃይል ያከማቸችው ባለፈው ወር የኢራን መንግስት በተቃዋሚዎች ላይ ደምአፍሳሽ እርምጃ ከወሰደና በቴህራንና ዋሽንግተን መካከል ያለው ውጥረት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ ነው።
ፕሬዝደንት ትራምፕ ኢራን በኑክሌር መርሃግብሯ ላይ ከአሜሪካ ጋር ስምምነት ላይ የማትደርስ ከሆነ “መጥፎ ነገሮች” ያጋጥሟታል በማለት በተደጋጋሚ ሲዝቱ ተደምጠዋል።

ኢራን በበኩሏ አሜሪካ ወደ ኃይል እርምጃ የምትገባ ከሆነ ከባድ የአጸፋ ምላሽ እንደምትሰጥና በቀጣናው የአሜሪካ ጦርን ያስጠጉ ሀገራት እንዲጠነቀቁ አሳስባለች።

Share this article

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው