ኢራን ሳኡዲ አረቢያ ውስጥ በልኡል ሱልጣን የአየር ኃይል ሰፈር ላይ በሰነዘረችው የሚሳይል ጥቃት 12 የአሜሪካ ወታደሮች መቁሰላቸውን የአሜሪካ ባለስልጣናት በትናንትናው እለት ተናግረዋል። በጥቃቱ ከተጎዱት ውስጥ ሁለቱ ወታደሮች በጽኑ መቁሰላቸውን ተዘግቧል።
እነዚህ ተጎጅዎች አሜሪካ ከእስራኤል ጋር በመቀናጀት በኢራን ላይ ጦርነት ከከፈተችበት ከፌብሩዋሪ 28 ጀምሮ ከቆሰሉት ከ300 በላይ የአሜሪካ ወታደሮች ተጨማሪ ናቸው።
አሜሪካና እስራኤል በከፈቱት መጠነሰፊ ጥቃት የኢራን ጠቅላይ መሪ አሊ ኻሚኒ፣ የጦር ባለስልጣናትና ከ1000 በላይ ንጹሃን ተገድለዋል።
ኢራንም በአጸፋ በእስራኤልና የአሜሪካን የጦር ሰፈሮች ባስጠለሉ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ላይ የድሮንና የሚሳይል ጥቃት በመሰንዘር ጉዳት እያደረሰች ነው። ኢራን ወሳኝ የነዳጅ ጫኝ መርከቦች መተላለፊያ የሆነውን የሆርሙዝ ባህረሰላጤን በመዝጋት የአለም የነዳጅ አቅርቦት እንዲስተጓጎልና ኢኮኖሚያዊ መናጋት እንዲደርስ አድርጋለች።
አሜሪካ፣ ኢራን ይህን መተላለፊያ ካልከፈተች በኃይል መሰረተልማቶቿ ላይ ጥቃት እንደምትሰነዝር ብታስጠነቅቃትም እስካሁን አልከፈተችም። የአሜሪካው ፕሬዝደንት ትራምፕ ግጭቱን በውይይት ለመፍታት ከኢራን ባለስልጣናት ጋር እየተወያዩ መሆናቸውን ቢገልጹም ኢራን ግን የተጀመረ ንግግር የለም ስትል አስተባብላለች።












