ወጣቷ የኬንያ የአየር ንብረት ተሟጋች ትሩፌና ሙቶኒ (Truphena Muthoni) አንድን ዛፍ ለ72 ተከታታይ ሰዓታት (ለሦስት ቀናት) በማቀፍ የራሷን የነበረውን የ48ሰዓታት የዓለም ሪከርድ በድጋሚ ሰብራለች። በጊነስ ወርልድ ሪከርድስ በይፋ የፀደቀላት ይህ ስኬት ከግል ዝና ይልቅ ትኩረት የሳበው ለአገሬው በቀል ዛፎችና ለአገሬው ተወላጆች ጥንታዊ እውቀት ባቀረበችው ጥልቅ ጥሪ ነው።
ትሩፌና እ.ኤ.አ በ2025 መጀመሪያ ላይ ለ48 ሰዓታት ዛፍ በማቀፍ ሪከርድ ይዛ የነበረ ቢሆንም በጋናዊ ተፎካካሪ ተሰብሮባት ነበር። አሁን ግን በኒየሪ ግዛት ለሦስት ቀናት ያህል ያለ እንቅልፍና ያለ ምግብ ዛፍን በመጠቅለል ክብረ ወሰኑን ወደ 72 ሰዓታት አሳድጋለች። ተሟጋቿ ይህንን ያደረገችው ሰዎች ከተፈጥሮ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲያድሱ ለማሳሰብ መሆኑን ትገልጻለች። “ሪከርዱን ለመስበር መነሳሳቴ ተፈጥሮን ከመትከላችን በፊት ልባችን ውስጥ ማሳደግ እንዳለብን ለማሳየት ነው” ትላለች ትሩፌና።
የአገር በቀል ዛፎችና የጥንታዊ እውቀት ጥበቃ
ትሩፌና እና መሰል የአፍሪካ የአየር ንብረት ተሟጋቾች አሁን ላይ ትኩረት እያደረጉ ያሉት “ዛፍ መትከል” ላይ ብቻ ሳይሆን “ምን ዓይነት ዛፍ?” በሚለው ላይ ነው። ኬንያ ውስጥ ከሚገኙ የዛፍ ዝርያዎች መካከል 13 በመቶው የመጥፋት አደጋ ተደቅኖባቸዋል። ትሩፌና የምታራምደው ንቅናቄ የውጭ አገር ዝርያ ያላቸው ዛፎች የአፈርን ለምነትና የውሃ ክምችትን ስለሚጎዱ እንደ “ሜሩ ኦክ” ያሉ አገር በቀል ዛፎች (Indigenous Trees) እንዲተከሉ ትወተውታለች።
ትሩፌና ለ72 ሰዓታት ዛፍ ስታቅፍ በቆየችበት ወቅት ለተወሰኑ ሰዓታት ዓይኗን በመሸፈን ለአካል ጉዳተኞችና ለጥንታዊ ማህበረሰቦች ያላትን አጋርነት አሳይታለች። ጥንታዊ ማህበረሰቦች ከተፈጥሮ ጋር ተስማምተው የመኖር ጥንታዊ እውቀት (Indigenous Knowledge) የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ወሳኝ መሆኑን ትገልጻለች።
የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ይህን አስደናቂ የትሩፌናን ተግባር በማድነቅ፣ ሀገሪቱ በ2032 15 ቢሊዮን ዛፎችን ለመትከል ለያዘችው ታላቅ ዕቅድ የአየር ንብረት አምባሳደር አድርገው ሾመዋታል። በተጨማሪም የሀገር መሪ አድናቆት (HSC) ሜዳሊያ ተሰጥቷታል።












