Loading...

የኒፓህ ቫይረስ ወቅታዊ ሁኔታ እና ስጋቶች

በደቡብ እስያ በተለይም በባንግላዴሽ እና በሕንድ የኬረላ ግዛት የኒፓህ ቫይረስ ስርጭት አሁንም ከፍተኛ የጤና ስጋት ሆኖ ቀጥሏል። በቅርብ ወራት ውስጥ በባንግላዴሽ በተከሰተ ወረርሽኝ ከ15 በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ አስሩ ሕይወታቸው አልፏል። ይህም የቫይረሱን አስከፊነትና ከፍተኛ የሞት ምጣኔ (ከ40% እስከ 75%) የሚያሳይ ነው። የዓለም ጤና ድርጅት ቫይረሱ ወደ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ የመቀየር አቅም ካላቸው ገዳይ በሽታዎች ተርታ መድቦታል።

እስካሁን በአዲሱ የአውሮፓውያን ዓመት (2026) በኒፓህ ቫይረስ ምክንያት የ10 ሰዎች ሕይወት ማለፉ የተመዘገበ ሲሆን ወረርሽኙ በተከሰተባቸው የባንግላዴሽ እና የሕንድ ኬረላ ግዛቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በለይቶ ማቆያ (Quarantine) ውስጥ ይገኛሉ። ቫይረሱ ተጨማሪ ስርጭት እንዳያሳይ በእነዚህ አካባቢዎች ጥብቅ የክትትል እና የለይቶ ማቆያ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው።

የኒፓህ ቫይረስ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ላይ የታወቀው እ.ኤ.አ. በ1999 በደቡብ ምስራቅ እስያ ማሌዢያ (Malaysia) ውስጥ ‘ካምፑንግ ሱንግጋይ ኒፓህ’ በተባለ መንደር ነው። በወቅቱ ወረርሽኙ የተከሰተው በከርከሮ አርቢዎች ላይ ሲሆን በሽታው ከከርከሮዎች ወደ ሰው መተላለፉ ተረጋግጦ ነበር። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ቫይረሱ በየዓመቱ ማለት ይቻላል በባንግላዴሽ እና በምሥራቅ ሕንድ አካባቢዎች ብቅ ማለቱን ቀጥሏል።

የበሽታው ስርጭት ምልክቶች እና የሕክምና ሁኔታ

የዚህ ቫይረስ ተፈጥሯዊ መገኛ “ፍራፍሬ በል የሌሊት ወፎች” (Pteropodidae family) ናቸው። የሌሊት ወፎቹ በቫይረሱ ቢጠቁም ራሳቸው ግን አይታመሙም። በሽታው ወደ ሰው የሚተላለፈው በቫይረሱ የተበከሉ ፍራፍሬዎችን ወይም ከሌሊት ወፍ የሚገኝን የተፈጥሮ ጭማቂ (ለምሳሌ የቴምር ጭማቂ) በመውሰድ ነው። በተጨማሪም በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ወይም እንስሳ (እንደ ከርከሮ) ጋር በሚኖር የቅርብ ንክኪና በሰውነት ፈሳሾች አማካኝነት በቀላሉ ሊሰራጭ ይችላል።

የኒፓህ ቫይረስ ምልክቶች እንደ ጉንፋን ባሉ ቀላል ሕመሞች ይጀምሩና በፍጥነት ወደ ከፋ የጤና ቀውስ ያመራሉ። ዋና ዋናዎቹ ምልክቶች ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ ሳል፣ የትንፋሽ ማጠር እና ማስመለስ ናቸው። በሽታው እየገፋ ሲሄድ ግን አእምሮን በማጥቃት (Encephalitis) ግራ መጋባትን፣ ማንቀጥቀጥን እና ታካሚው ወደ ራስ መሳት (Coma) ውስጥ እንዲገባ ያደርጋል። በአሁኑ ወቅት ለኒፓህ ቫይረስ የተረጋገጠ መድኃኒትም ሆነ ክትባት የሌለ ሲሆን የሚሰጠው ሕክምናም የታካሚውን ምልክቶች ለማስታገስና ሰውነቱን ለማጠናከር የሚደረግ ድጋፍ ብቻ ነው።

መከላከያ መንገዶች

እስከ አሁን ድረስ ለኒፓህ ቫይረስ በይፋ የጸደቀ ክትባትም ሆነ መድኃኒት የለም። ዋናው መከላከያ ንጽህናን መጠበቅ፣ ፍራፍሬዎችን አጥቦ መመገብ እና ከታመሙ ሰዎች ጋር የሚደረግ ንክኪን መቀነስ ነው።

Share this article

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው