ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዛሬው እለት በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ቀርበው የመንግስታቸውን የስድስት ወር የስራ አፈጻጻም ባቀረቡበት ወቅት በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለው ጸብ ተፋፍሞ “የመጨረሻው ጫፍ የደረሰው” በ2013 የተጀመረውን የትግራይ ጦርነት ያስቆመው የፕሮቶሪያ ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
“አንዳንድ ሰዎች በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ችግር የተፈጠረው የኢትዮጵያ መንግስት የቀይ ባህር ጥያቄ ስላነሳ ነው ብለው ያስባሉ፣ ይተነትናሉ። ግን አይደለም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጸቡ ኤርትራ ስትፈጠር የጀመረና እሳቸው ወደ ስልጣን ሲመጡ ችግሩን ለመፍታት እንደለመኑ ጠቅሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት “እንዴት ህወሓት ሳይጠፋ፣ እንዴት ትግራይ ሳትወድም” ስምምነት ይደረጋል በሚል የኤርትራ መንግስት ከፍተኛ ቅሬት አድሮበታል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኤርትራ ጦር በመጀመሪያው ዙር የኢትዮጵያ መንግስትና የህወሓት ኃይሎች ጦርነት ወቅት የኤርትራ ጦር በትግራይ የተለያዩ አካባቢ ግድያና ዘረፋ ፈጽሟል የሚል ጠንካራ ክስ አሰምተዋል።
አለምአቀፍ የመብት ተሟጓች ተቋማት በጦርነቱ ወቅት የኢትዮጵያን ጦር ደግፎ ወደ ትግራይ ክልል የገባው የኤርትራ ጦር የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽሟል የሚል ክስ አቅርበው የነበረ ቢሆንም የኤርትራ መንግስት አስተባብሏል። ኤርትራ የፕሪቶሪያውን ስምምነት የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ አድርጋ እንደምታየውና ቅር አለመሰኘቷንም በማስታወቂያ ሚኒስትሩ የማነ ገብረመስቀል በኩል መግለጿ ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በጦርነቱ ወቅት የኤርትራ ጦር የኢትዮጵያን ጦር እየተከተለ በአክሱም ወጣቶችን መግደሉን በአድዋና አዲግራት የንብረት ዝርፊያ መፈጸሙን ገልጸዋል። የኤርትራ ጦር ወደ መቀሌ ገብቶ ጥፋት እንዳይፈጽም ውቅሮ ላይ ኬላ ተጥሎ እንደነበርም ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለው እንዳሉት በዚህ ምክንያት ጸቡ “ከህወሓት እንጅ ከትግራይ ህዝብ” ባለመሆኑ የኤርትራ ጦር ግድያና ዘረፋ እንዲያቆም ሽማግሌ ልከው ነበር።
አክራሪ ያሏቸው የህወሐት ኃይሎች ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከኤርትራ ጋር እየሰሩ ነው የሚል ክስ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የፕሪቶሪያው ሲፈረም የኢትዮጵያ ጦር መቀሌ ለማግባት አንድ ቀን የቀረውና ጦርነቱን ያሸነፈ ቢሆንም ህዝብ እንደይጎዳ በሚል እንደተወው ተናግረዋል።
የኤርትራን መንግስት ጨምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ ችግር ለመፍጠር ለታጣቂዎች ፋይናንስ የሚያደርጉ ጠላቶች አሉ፤ ነገርግን አይሳካላቸውም ሲሉም ተደምጠዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ምርጫ 2018
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የዘንድሮ ምርጫ ከባለፈው ምርጫ የተሻለ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና አካታች ይሆናል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
“አንድ ፖርቲ ብቻ ለኢትዮጵያ አይጠቅምም” የሚል አቋም እንዳላቸው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣይ ምርጫ የተቃዋሚዎች ድምጽ ከ5-10 በመቶ ያድጋል ብለው ያምናሉ። መንግስት ስራውን ትቶ ጊዜና ገንዘቡን ምርጫ ላይ እያዋለ ነው የሚለውን ትችትም ተከላክለዋል።
የመንግስት ሚዲያዎች የሁሉንም ፓርቲዎች ድምጽ የሚያስተጋቡ መሆን ይኖርባቸዋል ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም እንዳሉት ምርጫው ልክ ሃይማኖታዊ በዓላት ሁሉ ሰላማዊ ሆኖ ይጠናቀቃል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ ጉዳይ
በአፍሪካ ቀንድ ያለ ህዝብ በባህል፣ በቀንቋና በዘር የተሳሰረ እንዲሁም ብዙ ሀብቶች የታደለ ከባቢ ቢሆንም ከፍተኛ ፉክክሮችና የውጭ ጣልቃገብነቶች ችግር እየፈጠሩ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ።
“የሁለቱ ውሃዎች(የቀይ ባህርና የናይል) ጉዳይ እኛንም እያተራመሰ በእኛ ጉዳይ የሚገቡ ኃይሎችንም እያሰፋ በመሄዱ አንዱ ጎረቤት ለሌላኛው ጋሻ መሆን ሲገባው ጥይት አቀባይ ሆኗል” ሲሉ ተደምጠዋል።
ቀጣናው ከእንዲህ አይነት ችግር እንዲወጣ እየሰሩ መሆናቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የባህር በር የማግኘት ለኢትዮጵያ የብሔራዊ ደህንነት ጉዳይ መሆኑን አስምረው ተናግረዋል።
“ቀይ ባህርና ኢትዮጵያ ለዘላለም ተነጣጥለው መኖሮ አይችሉም።”
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ከምጽዋ እስከ ሞጋዲሹ 5000ኪሎሜትር የሚረዝም የባህር ጠረፍ 20 ሚሊየን ገደማ በሚሆን ህዝብ የተያዘ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ 130 ሚሊየን ህዝብ ያላት ኢትዮጵያ የጠየቀችው 50 ኪሎሜትር ጠረፍ ይገባታል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ ለባህር በር ተጋሪ ሀገራት ከህዳሴ ግድና ከኢትዮጵያ አየርመንገድ ሸር በመስጠት ወይም መሬት በመቀየር የባህር ብር ለማግኘት መደራደር እንደምትፈልግ በድጋሚ ተናግረዋል።












