የናሳ አርቴሚስ 2 (Artemis ll) ጠፈርተኞች ከመሬት ረጅም ርቆ በመጓዝ ከዚህ በፊት ተይዞ የነበረውን ክብረወሰን በመስበር ታሪክ ስርተዋል።
በኦሮሪዮን መንኮራኩር የመጠቁት አራቱ ጠፈርተኞች ከዚህ በፊት የነበረውን የ400,171 ኪሎሜትር (248,655 ማይልስ) ርቀት ክብረወሰን ባለፈው ሰኞ መስበር ችለዋል። ይህ ክብረወሰን በአፖሎ 13 የተያዘው እኤአ በ1970 ነበር።
ጠፈርተኞቹ 252,756 ማይሎች በመጓዝ የአፖሎን ክብረወሰን ከ4000 በላይ በሆኑ ማይሎች አሻሽለውታል።
መንኮራኩሯ ጨረቃን በመዞር በምታደርገው በረራ ላይ ጠፈርተኞቹ ከስድስት ሰዓት በላይ የጨረቃን ገጽታ በማጥናትና መረጃዎችን በመመዝገብ አልፈዋል። በመቀጠልም የኦርዮን ካፕሱል ወደ ምድር ለመመለስ የአራት ቀናት ጉዞ ይጀምራል።
ጠፈርተኞቹ ይህን ታሪካዊ ቀን የጀመሩት በአፖሎ 8 እና 13 ተልዕኮዎች ተካፋይ የነበሩ ጂም ላቭል ህይወታቸው ሊያልፍ ጥቂት ሲቀራቸው ባስተላለፉትና ተቀርጾ በተቀመጠ መልዕክት ነበር። ላቭል “ታሪካዊ ቀን ነው፤ ውጥረት እንደሚበዛባችሁ አውቃለሁ፤ ነገር ግን እይታውን መደሰት እንዳትረሱ። ወደ አሮጌው መንደሬ እንኳን ደህና መጣችሁ። ጨረቃን ስትዞሩ ይህን ችቦ ለእናንተ በማስተላለፌ ኩራት ይሰማኛል”ብሏል።

ጠፈርተኞቹ ከጨረቃ በስተጀርባ በኩል በሚጓዙበት ወቅት ከዚህ ቀደም ተሰውሮ የነበረውን የጨረቃ ክፍል ተመልክተዋል። ከጠፈርተኞቹ የተላከ አንድ ምስል “ኦሬንታሌ ቤሲን” (Orientale basin) የተባለውን ግዙፍ ጉድጓድ ያሳያል። ይህም ከዚህ ቀደም ሰው አልባ በሆኑ መንኮራኩሮች ካሜራ ብቻ የታየ ነበር። ናሳ ምንም እንኳን የቴክኖሎጂ እድገት ቢኖረውም፣ ስለ ጨረቃ የበለጠ ለማወቅ አሁንም በጠፈርተኞቹ ምልከታ ላይ ይተማመናል።
የአርቴሚስ 2 ዋና ሳይንቲስት ኬልሲ ያንግ ለኤኤፍፒ (AFP) እንደተናገሩት “የሰው ልጅ አይን እስካሁን ከተሰሩትና ወደፊትም ከሚሰሩት ካሜራዎች ሁሉ የተሻለ ነው” ብለዋል።
በሂውስተን ቴክሳስ በሚገኘው የናሳ ጆንሰን ስፔስ ሴንተር ውስጥ የሚገኙ በደርዘን የሚቆጠሩ የጨረቃ ሳይንቲስቶች፣ ጠፈርተኞቹ የሚያዩትን ነገር በቀጥታ ሲያብራሩና ማስታወሻ ሲይዙ ነበር።
በአዛዥ ሪድ ዊስማን የሚመራው የአርቴሚስ 2 ቡድን በርካታ “የመጀመሪያ” የተባሉ ታሪኮችን ይዟል። ቪክቶር ግሎቨር ጨረቃን በመዞር የመጀመሪያው ጥቁር ሰው ሆኗል። ክሪስቲና ኮክ የመጀመሪያዋ ሴት ሰትሆን ካናዳዊው ጄረሚ ሀንሰን ደግሞ የመጀመሪያው አሜሪካዊ ያልሆነ ጠፈርተኛ ናቸው።
መንኮራኩሯ በጨረቃ በስተጀርባ ስታልፍ ጠፈርተኞቹ ምድር ካለው ማዕከል ያላቸው ግንኘነት ለ40 ደቂቃ አካባቢ ተቋርጦ ነበር።ይህ እድግ የሚያስገርም ሆኖ ተመዝግቧል።
በናሳ የፕላኔቶች ጂኦሎጂ ላብራቶሪ ኃላፊ ኖህ ፔትሮ እንደገለጹት፣ ጨረቃ ለጠፈርተኞቹ “በእጅ የተያዘ የቅርጫት ኳስ ያህል” ሆና ትታያቸዋለች።
ይህ በረራ እ.ኤ.አ. በ2027 ለሚካሄደው አርቴሚስ 3 እና በ2028 ለሚጠበቀው በጨረቃ ላይ የማረፍ ተልዕኮ (አርቴሚስ 4) ትልቅ ዝግጅት መሆኑን የናሳ አስተዳዳሪ ጃሬድ አይዛክማን ገልጸዋል።












