Loading...

ሴኔጋል የአፍሪካ ዋንጫን አነሳች

ሴኔጋል ሞሮኮን አሸንፋ ለሁለተኛ ጊዜ ዋንጫ ማንሳት ብትችልም፣ በሞሮኮው ልኡል አብደላ ስቴዲየም የታየው ትርምስ ጨዋታውንና ድሉን አደብዝዞታል።

ውዝግቡ የተነሳው በመደበኛው የጨዋታ ማብቂያ ላይ ዳኛው ለአስተናጋጇ ሞሮኮ ፍጹም ቅጣት ምት ከሰጠ በኋላ የሴኔጋል ተጨዋቾች በተቃውሞ በጊዜያዊነት ከሜዳ መውጣታቸው ተከትሎ ነበር።

ጨዋታውን የመሩት ዋና ዳኛ ጂን ጃኩየስ ነዳላ የቪዲዮ ረዳት ዳኛውን ካማከሩና የሴኔጋል ተከላካይ ኢል ሀድጂ ማሊክ በብራሂም ዳይዝ ላይ የሰራውን ጥፋት ካዩ በኋላ በ98ኛው ደቂቃ ላይ ፍጹም ቅጣት ምት ሰጡ።

ቀደም ሲል የሴኔጋልን ግብ በሻሩት ዳኛ ተበሳጭተው የነበሩት ዋና አሳልጣኝ ቡድናቸው ከሜዳ እንዲወጣ አደረጉ። የቀድሞው የሊቨርፑል ተጨዋች የሆነው ሳዲዮ ማኔ ከሜዳ ሳይወጣ የቡድን አጋሮቹ ጨዋታውን እንዲጨርሱ ሲያበረታታ ታይቷል። በመጨረሻም ከ17 ደቂቃ መዘግየት በኋላ ተጨዋቾቹ ወደ ሜዳ ሊመለሱ ችለዋል።

እምነት የተጣለበት የሪያል ማድሪዱ አጥቂና የውደድሩ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ዲያዝ የመታው ፍጹም ቅጣት ምት ብዙም እንቅስቃሴ ባላሳየው የሴኔጋሉ ግብ ጠባቂ ኢድዎርድ ሜንዲ ከሸፈበት። ዳኛውም የጨዋታው መደበኛ ሰአት መጠናቀቁን በፊሽካቸው አወጁ።

የሴኔጋሉ አማካኝ ተጨዋች ፔፕ ጉዩ  የጭማሪ ደቂቃ (ኤክስትራ ታይም) ጨዋታ በተጀመረ በአራተኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ግብ  አንበሶቹ በአምስት አመታት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ዋንጫ እንዲያነሱ አስችሏቸዋል።

የሞሮኮው አሰልጣኝ ዋሊድ ሬግራጊ ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ በሰጡት ቃለምልልስ የሴኔጋልን ድርጊት አሳፋሪና ለአፍሪካ ክበር የማይመጥን ነው ሲሉ ተናግረዋል። የሴኔጋሉ አሰልጣኝ ቲያው በፕረስ ክፍሉ ውስጥ በነበረው ትርምስ ምክንያት መግለጫውን ሰርዟል።

ነገርግን ቲያው ለቤንስፖርት በሰጠው ቃለምልልስ ተጨዋቾቹ ሜዳ ለቀው እንዲወጡ ማዘዙ ትክክል እንዳልነበር አምኗል።
“ማድረግ አልነበረብንም፤ ነገርግን ሆኗል። አሁን ይቅርታችንን ለእግርኳስ እናቀርባለን” ብሏል።

Share this article

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው