Loading...

ምዕራባውያን መንግስታት በታንዛኒያ የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች ላይ ምርመራ እዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል

በርካታ የአውሮፓ ሀገራት፣ አሜሪካ እና ካናዳ፥ በታንዛኒያ በቅርቡ የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ ተፈጽሟል የተባሉ የሰብአዊ መብት ረገጣዎችን የተመለከተ መግለጫ አውጥተዋል።

እንግሊዝ፣ ኖርዌይ፣ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት እና ካናዳ በጋራ መግለጫቸው የተቃዋሚ ፖለቲከኞች እስር፣ ከፍርድ ወጭ ግድያዎችን እና አስከሬኖችን አለመመለስ የመሳሰሉ የመብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን ገልጿል። አገራቱም ለታንዛንያ መንግስት መሰረታዊ ነፃነቶችን እንዲያከብር ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።

መግለጫው ባለስልጣናት እስረኞችን እንዲፈቱ፣ የተደበቁ አስከሬኖችን ወደ ቤተሰብ እንዲመልሱ እና ሁሉም እስረኞች የህግ ውክልና እና የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ አሳስቧል።

የጋራ መግለጫ ሁከቶችን ያስነሱ ምክንያቶች ከስር መሰረታቸው ለማጣራት፥ ገለልተኛ እና ግልፅ የሆነ ምርመራ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ የእምነት አካላት እና የፖለቲካ ተዋናዮች ተሳትፎ እንዲደረግ የታንዛኒያ መንግሥትን ጠይቋል።

አሜሪካም ከታንዛኒያ ጋር ያላትን ግንኙነት በተመለከተ የራሷን ግምገማ አውጥታለች። የአሜሪካ ስቴት ዲፓርመንት ቃል አቀባይ ቶሚ ፒገት፥ በግምገማው በታንዛንያ አሁንም እየቀጠለ ባለው ጭቆና እና የመብት ጥሰቶች ምክንያት “ታንዛንያ እንደ አጋር አገር የማንተማመንባት ሆናለች” ብለዋል። መግለጫው ከመብት ጥሰቶች በተጨማሪ በአሜሪካ የኢንቨስትመንት ፍላጎቶች እና በሀገሪቱ ውስጥ ባሉ የአሜሪካ ዜጎች እና ቱሪስቶች ላይ የተጋረጠው የደህንነት አደጋ እንዳሳሰበው ይገልጻል።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ (የአውሮፓ ህብረት ፣ የሲቪል ማህበረሰብ ፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች) ከምርጫው በኋላ ወዲያውኑ በታንዛንያ የተፈጸሙ የመበት ጥሰቶችን ያወገዘ ቢሆንም፥ አዲሱ የጋራ ዲፕሎማሲያዊ መግለጫ እና የአሜሪካ ግምገማ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀናጀ የጋራ ጫና የተደረገበት ሆኗል።

Share this article

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው