የአሜሪካ ፍርድ ቤት ዳኛ የፕሬዝደንት ትራምፕ አስተዳደርን በአሜሪካ ለሚኖሩ በሺዎች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ተሰጥቶ የነበረውን ያለመባረር ከለላ የማቋረጥ ውሳኔ በጊዜያዊነት እግድ ጥሎበታል።
በቦስተን የአሜሪካ ዲስትሪክት ዳኛ ብሬን ሙርፊይ የአሜሪካ የሀገር ውስጥ ደህንነት መስሪያ ቤት (ዲፓርትመንት ሆምላንድ ሴኩሪቲ) የ5000 ኢትዮጵያውያን ጊዜያዊ ከለላ ማብቃት ተፈጻሚ የሚሆንበት የካቲት 13፣2026 እንዲዘገይ ትዕዛዝ እንደሚሰጡ ተናግረዋል። ዳኛው ይህን ያደረጉት የህግ ጉዳዮች እንዲታዩ ተጨማሪ ጊዜ ለመስጠት ነው።
የደህንነት መስሪያ ቤቱ ጊዜያዊ ከለላውን ለማንሳት የወሰነው በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ ከገመገመና ኢትዮጵያውያን በዚህ መብት ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችላቸውን መስፈርት እንደማያሟሉ በመግለጽ ነበር።
በዲሞክራቱ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር የተሾሙት ዳኛ ሙርፊይ በችሎት እንደተናገሩት ተግባራዊ የሚሆንበት ቀን እንዲዘገይ ያደረጉት የደህንነት መስሪያ ቤቱ ውሳኔውን እንዴት እንዳሳለፉ ዝርዝር ማስረጃ እንዲያቀርብ ለማስቻልና አስፈላጊ ከሆኖ ከተገኘ እግዱን ለማራዘም ነው።
የደህንነት መስሪያ ቤቱ በስደተኞች መብት ተሟጋቾች ለቀረበበት ክስ ምላሽ ለመስጠት ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል። ከለላው እንዳያበቃ በፍርድ ቤት የተላለፈውን ጊዜያዊ እግድም የደህንነት መስሪያ ቤቱ ተቃውሞታል።
ዳኛው እንደገለጹት የመንግስት ጠበቃ በአንድ ሳምንት ውስጥ ይቀርባል ያለው የደህንነት መስሪያ ቤቱ መረጃ ከቀረበ በኋላ ተጨማሪ ክርክር የሚደረግበትን ጊዜ ያሳውቃሉ።
“ይህን ጉዳይ ለማስቀጠል ሁሉንም ነገር መስራት እፈልጋለሁ” ብለዋል ሙርፊይ።
የደህንነት መስሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ትሪሺያ ማክላፍሊን ባወጡት መግለጫ ጊዜያዊ ከለላው ዘለቄታዊ የምህረት መርሃግብር እንዲሆን ታስቦ ባይጀመርም፣ የቀድሞ አስተዳደሮች ግን ለአስርት አመታት እንደዚያ ሲጠቀሙቀት ቆይተዋል ብለዋል።
በአሜሪካ ፌደራል ህግ መሰረት በጊዜያዊነት ከአሜሪካ ያለመባረር ከለላ(ቴምፖራሪ ፕሮቴክሽን ስታተስ) የሚሰጠው ስደተኞቹ የመጡበት ሀገር ውስጥ የተፈጥሮ አደጋ፣ ግጭት ወይም ሌላ የተለየ ሁኔታ ሲኖር ነው። መንግስት ይህን ለሚያሟሉ ስደተኞች የስራ ፈቃድና እንዳይባረሩ ከለላ ይሰጣል።
ፕሬዝደንት ትራምፕ በስተደኞች ላይ እየወሰዱ ያሉት ጠንካራ ውሳኔ ተከተሎ የደህንነት መስሪያ ቤቱ አስር ገደማ የሚሆኑ ሀገራትን ስደተኞች ከለላን ለማንሳት ተንቀሳቅሷል።












