በቅርቡ ተሰናባች የሚሆኑት የግብጽ መከላከያ ሚኒስትር ጄኔራል አብደል ማጂድ ሳቅር እንዲሁም የጦር ኃይሎች ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል አህመድ ካሊፋ ከሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼኽ መሀሙድ ጋር በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ስር የተመደቡ የግብፅ ወታደሮችን የዝግጅት ትርዒት ታድመዋል።
በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ (AUSSOM) ስር የተደራጀው ይህ ኃይል ፈንጂ መከላከያ የተገጠመላቸው (MRAP) ከባድ እና ቀላል ተሽከርካሪዎች፣ ተዋጊ እና የቁሳ ቁስ ማጓጓዣ ሄሊኮፕተሮች እና ሌሎችም የጦር መሳሪያዎችን አካቷል።
የጦር ዝግጅቱ የተካሄደው የግብጹ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ ኤል ሲሲ በAUSSOM እንዲሁም በሌሎች የሁለትዮሽ እና በቀጠናው እየተፈጠሩ ያሉ ለውጦችን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ከሶማሊያው ፕሬዝዳንት ጋር እሁድ እለት በካይሮ ባደረጉት ስብሰባ ላይ ከተወያዩ በኋላ ነው።
ኤል ሲሲ ውይይቱን ተከትሎ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ግብፅ በሶማሊያ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ያላትን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።
ግብጽ እና ሶማሊያ እ.ኤ.አ በ2024 የሁለትዮሽ የጦር ትብብር ከተፈራረሙ በኋላ ግብጽ አስር ሺህ ወታደሮችን በሶማሊያ ማስፈር ግብ አድርጋ የመጀመሪያዎቹን ወታደሮች ወደ ሶማሊያ መላኳ ይታወሳል።
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረሙትትን የመግባቢያ ሰነድ(MOU) ተከትሎ መጠናከር የጀመረው የግብጽ ለሶማሊያ የሚቀርብ ወታደራዊ ድጋፍ፥ ከቅርብ ሳምንታት በፊት እስራኤል ለሶማሊላንድ እውቅና መስጠቷ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ የባህር መተላለፊያ ለማግኘት የምታደርገው ጫና መቀጠሉ እና በኢትዮጵያ እና ግብጽ መሃል የቀጠለው የታላቁ ህዳሴ ግድብ(GERD) አለመግባባት ግብጽ በሶማሊያ ኃይሏን ይበልጥ እንድታጠናክር ምክንያት እንደሆነ የአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ተንታኞች ይገልጻሉ።

















