የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) የዘንድሮውን የአለም አቀፍ የጤና ሽፋን (UHC) ቀን ሲያከብር፣ “ኪካሰቸው አውጥተው መክፈል ለማይችሉ የጤና አገለግሎትን በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ” ዋና አጀንዳው አድርጓል። የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ካለፈው ህይወታቸው ጥልቅ የሆነ የግል የታሪከ አጋጣሚን በማካፈል የህክምና አገልግሎት ውደነትን የመፍታት አስፈላጊነት ምን ያህል እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተው አስረድተዋል። ለህክምና የተጠየቀውን ከፍተኛ ገንዘብ በመክፈል እዳውን ቤተሰቡ ላይ ከመጫን ይልቅ ሞትን ለመቀበል የመረጠ የካንሰር ታማሚ የነበረ የቅርብ ጓደኛ እንደነበራቸው ዶክተር ቴዎድሮስ ተናግረዋል። “ጓደኛዬ የሚወደው ቤተሰቡን ከእድሜ ልክ ዕዳ እንደሚታደጋቸው በማመኑ እና የወደፊት ህይወታቸውን ከገንዘብ ችግር ነፃ ለማደረግ በመምረጡ ነበር ያንን ያደረገው።” ይላሉ ዶ/ር ቴዎድሮስ። የጤና አገልግሎት ውድ መሆኑ የሚያስከትለውን አስከፊነት ከግል ህይወታቸው ምሳሌን በማንሳት “ማንም ሰው እንደዚህ አይነት ምርጫ እንዲያደርግ መገደድ የለበትም” በማለት በአጽንዖት ያሳስባሉ።
በመግለጫቸው በአለም ዙሪያ 4.6 ቢሊዮን ሰዎች አስፈላጊውን የጤና አገልግሎት እንደማያገኙ እና 2.1 ቢሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ለምግብ ፣ ለትምህርት እና ለመጠለያ ቤት ከሚያውሉት ወጪ ተርፏቸው፥ ለህክምና አገልግሎት ለመክፈል የሚያስችል የገንዘብ ችግር እንዳለባቸው ተናግረዋል። የዓለም ጤና ድርጅት እነዚህን ክፍተቶች ለማጥበብ ከሃገራት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። “ጤና አቅም ላላቸው ሰዎች ብቻ የተሰጠ የቅንጦት ነገር ሳይሆን ለሁሉም ሰው መሰረታዊ መብት መሆን አለበት” ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ።
የዘንድሮው የአለም አቀፍ የጤና ሽፋን (UHC) ቀን በዲሴምበር 12 ቀን 2025 የተከበረ ሲሆን፥ የዚህ አመት አጀንዳ ተመጣጣኝ ያልሆነ የጤና አገልግሎት ወጪን መቀነስ ላይ ያተኮረ ሆኗል። ድርጅቱ፥ ዝቅተኛ ገቢ ወይም ሥር የሰደደ በሽታ ላለባቸው ሰዎች ያልተመጣጠኑ የጤና አገግሎት ወጪዎችን ለማስወገድ አስቸኳይ እርብርብ እንዲደረግ ጠይቋል።












