የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) በናይሮቢ ኬንያ የሚገኘውን ቢሮውን ማስፋፊያ ግንባታ በ340 ሚሊየን ዶላር አስጀምሯል። ይህ ድርጅቱ ከተመሰረተ ወዲህ በአፍሪካ ከሰራቸው ግዙፍ የመሰረተልማት ኢንቨስትመንቶች አንዱ ነው።
የተመድ ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ከኬንያው ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ ጋር በመሆን በጊጊሪ አካባቢ በሚገኘው የተመድ የናይሮቢ ቢሮ (UNON) በተካሄደው የአዲሱ የስብሰባ ኮምፕሌክስ የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጥ ስነስርዓትና የዘመናዊ የቢሮ ህንጻዎች ምርቃት ላይ ተገኝተዋል። ይህ ማስፋፊያ ተመድ በአፍሪካ ያለውን ቦታ በእጅጉ እንዲጨምር ለማድረግ ታስቦ እንደሆነ ተገልጿል።
ፕሮጀክቱ የ265.7 ሚሊዮን ዶላር የመሰብሰቢያ ማዕከላት ማሻሻያና የ66.2 ሚሊዮን ዶላር ከአየር ንብረት ጋር ተስማሚ የሆኑ የቢሮ ህንጻዎችን ግንባታ የሚያካትት ሲሆን ይህም ናይሮቢ በአለም ወሳኝ ከሆኑት የተመድ ማዕከላት አንዷ እንድትሆን ያደርጋታል።
እንደተመድ ከሆነ ማስፋፊያው ተመድ በናይሮቢ ኮምፕሌክሱ ያሉን የመሰብሰቢያ ቢሮዎች ከ14 ወደ 30 የሚያሳድግ ሲሆን የመቀመጫ አቅሙን ደግሞ አዲሱንና 1600 መቀመጫ ያለውን የመሰብሰቢያ አዳራሽ ጨምሮ ከ2000 ወደ 9000 ከፍ ያደርገዋል። ኢንቨስትመንቱ ናይሮቢን ከኒው ዮርክና ከጄኔቫ ቀጥሎ ሶስተኛዋ የተመድ አለምአቀፍ መዳረሻ ያደርጋታል ተብሎ ይጠበቃል።

እያደገ የመጣው የአፍሪካ ተጽዕኖ
ጉተሬዝ የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ የአፍሪካ ተጽዕኖ በተመድና በአለምአቀፍ ዲፕሎማሲ እያደገ መምጣቱን የሚያሳይ ነው ብለዋል። የናይሮቢ ዋና መቀመጫ ከዚህ በኋላ እንደዳር የሚታይ መሆኑ እንደሚያበቃ ጉተሬዝ ተናግረዋል።
“ናይሮቢ ተራ ቢሮ ወይም ጫፍ አይደለችም። በአፍሪካና በደቡባዊ ንፍቀክበብ የተመድ ዋና መቀመጫ ምሰሶ ነች።”
ዋና ጸኃፊው ጉተሬዝ እንዳሉት ማስፋፊያው ድርጅቱ ከአፍሪካ ጋር ያለው ግንኙነት መለወጡን የሚያሳይ ነው። ይህ ማስፋፊያ ድርጅቱ “ለህዝብና ለሚያገለግለው ቀጣና ቅርብ ለመሆን” ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።
የኬንያ መንግስት በትናንትናው እለት ባወጣው መግለጫ ፕሮጀክቱ ናይሮቢ “በደቡባዊ ንፍቀክበብ ብቸኛዋ የተመድ ዋና መቀመጫነቷን የሚያጠናክርና ኬንያ በአለምአቀፍ ዲፕሎማሲ፣ በባለብዙ ወገን ግንኙነትና በዘላቂ ልማት ያላት ሚና እየጨመረ መምጣቱን የሚያረጋግጥ ነው”ብሏል። አዳሱ የስብሰባ ኮምፕሌክስ ዲዛይን ተደራሽነትን፣ አካባቢያዊ ዘላቂነትንና የስብሰባ አቅምን ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ የገለጹት ባለስልጣናቱ የናይሮቢን የዲፕሎማሲና የሂውማኒተሪያን ማዕከል የመሆን ህልም የሚደግፍ ነው ብለዋል።
በአሁኑ ጊዜ በናይሮቢ ያለው የተመድ ቢሮ ከ4,000 በላይ ሰራተኞችን እና 88 ቢሮዎችን ይዟል። ድርጅቱ በኬንያ ውስጥ በአጠቃላይ ወደ 6,000 የሚጠጉ ስራተኞች አሉት።
የጊጊሪ ኮምፕሌክስ የኬንያ መንግስት ለተመድ በሰጠው 140 ኤከር (56.6 ሄክታር) መሬት ላይ ይገኛል። ይህም በአስተናጋጅ ሀገር ለድርጅቱ የተበረከተ ትልቁ የመሬት ስጦታ ነው።
የኬንያ መንግስት በመሠረተ ልማት፣ በአካባቢ ማሻሻያ እና በደህንነት ማጠናከሪያዎች ላይ ኢንቨስትመንት በማድረግ የናይሮቢን አለምአቀፋዊነት ለማሻሻል እንደሚራ አረጋግጧል።












