እ.አ.አ. ከሜይ 1፣2026 ጀምሮ የሚተገበረው አዲሱ የቻይና የዜሮ ታሪፍ (የቀረጥ ነጻ) ፖሊሲ ኢትዮጵያን ጨምሮ 53 የአፍሪካ ሀገራትን የሚያካትት ነው። ይህ ፖሊሲ አበባን ጨምሮ የሆርቲካልቸር ምርቶችን ያለ ቀረጥ ወደሰፊው የቻይና ገበያ ለመላክ ያስችላል።
የቻይና ገበያ ሰፊ ፍላጎት(400 ሚሊዮን ገዥዎች) ያሉበት በመሆኑ ለአበባ አምራቾችና ላኪዎች ወሳኝ ገጸ-በረከት ተደርጎ የሚታይ ነው።

ፖሊሲው የኢትዮጵያን የአበባ ንግድ መዳረሻ ትርጉም ባለው መልኩ ያሰፋል። ቀደም ሲል የኢትዮጵያ የአበባም ሆነ አጠቃላይ የሆርቲካልቸር ምርት ሽያጭና ምርት የአውሮፓ ሀገራት ገበያን ታሳቢ ያደረገ ነበር። ነገርግን አሁን የቻይና መንግስት የሚተገበረው የዜሮ ታሪፍ ፖሊሲ ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ገበያ ጥገኝነት እንድትላቀቅና መዳረሻዋን እንድታሰፋ (diversity) በር ይከፍታል።
አማራጭ የገበያ መዳረሻዎች እንደ ኮቪድ-19 ያሉ አለምአቀፋዊ ነውጦች (shocks) በሚፈጠሩበት ጊዜ ገበያውን ከከፍተኛ መዋዠቅ ይታደጋሉ።

ኢትዮጵያ ለአበባ ምርት ምቹ የምትባል ሀገር ነች። ለማምረት የሚወጣው ወጭ( cost of production) ዝቅተኛ መሆኑ እና ተስማሚ የአየር ንብረት መኖሩ ኢትዮጵያ በአበባ ምርት ከሌሎች ሀገራት ጋር ተፎካካሪ እንድትሆን ያስችላታል።
የኢትዮጵያ አየርመንገድ ደግሞ ምርት የማጓጓዝ አገልግሎት በመስጠት የሎጂስቲክ ክፍተቱን ይሞላል። አየርመንገዱ ወደ ቻይና የሚያደርገው ሳምንታዊ በረራና መዳረሻ ከተሞቹ መጨመራቸው የኢትዮጵያን የአበባ ምርት ወደ ቻይና ገበያ ለማድረስ ሁነኛ አጋጣሚ ይሆናል። በሳምንት ውስጥ ወደ ቻይና ከ60 በላይ በረራዎችን የሚያደርገው አየር መንገዱ፣ የአበባ ምርትን በቀጥታ ወደ ቻይና በመጫን ንግዱን የማቀላጠፍ ሚና ይጫወታል።

ይህ ፖሊሲ ለኢትዮጵያ አበባ አምራቾችና ላኪዎች ትልቅ ብስራት ነው የሆነላቸው።
የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራቾችና ላኪዎች ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ቴዎድሮስ ዘውዴም በዚህ ይስማማሉ። ቻይና ይህን በመፍቀዷ መደሰታቸውንና ይህን ልዩ እድል ለመጠቀም ዝግጅት እየተገረገ እንደሆነ ይናገራሉ።
አቶ ቴዎድሮስ ፖሊሲው የስራ እድልን ለመፍጠርና የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ ወሳኝ ነው የሚል ጠንከር ያለ ሀሳብ ያራምዳሉ።
የአበባ ምርት ላኪዎችም የአቶ ቴዎድሮስን ሃሳብ ይደግፉሉ። የአፍሪ ፍላወር (Afriflower) ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ስንታየሁ ከበደ ኩባንያቸው የአበባ ምርቶችን ወደ ቻይና በመላክ ከዜሮ ታሪፍ እድሉ ለመጠቀም እንዳቀደ ተናግረዋል። ይህን እድል ለመጠቀም የጓጉት አቶ ስንታየሁ ብቻ አይደሉም፤ ብዙዎች የሚጀመርበትን እየጠበቁ ናቸው።

እድሉ አምራቾች የበለጠ እንዲያመርቱ ላከዎች ደግሞ የሚልኩትን መጠን እንዲጨምሩ የሚያበረታታ ነው። ይህ ደግሞ በዘርፉ ሰፊ የስራ እድል እንዲፈጠር እንዲሁም የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ክፍተት እንዲቃለል አይተኛ ሚና ይጫወታል።
በጥቅሉ ሲታይ ይህ የዜሮ ታሪፍ ፖሊሲ ለኢትዮጵያ ትልቅ እድል ይዞ መጥቷል። ታዲያ ይህን እድል ለመጠቀም ኢትዮጵያም ምርቶቿን ማስተዋወቅና የጥራት ደረጃውን የጠበቀ ምረት ለገበያ ማቅረብ ይጠበቅባታል። የሚላኩ ምርቶችን የቻይናን የጥራትና የጤና መመዘኛዎችን ማሟላት አስፈላጊ ይሆናል። እድሉን በአግባቡ ለመጠቀም መንግስትና አምራች የሆነው የግሉ ዘርፍ ተባብረው መስራት ይኖርባቸዋል። እድሉ ሰፊና ክፍት ቢሆንም እድሉን መጠቀም ግን በኢትዮጵያ ዝግጅት ላይ የተሰረተ ነው። ፖሊሲው ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ባሻገር የኢትዮጵያና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የበለጠ እንዲጠነክር የራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታል።
እ.ኤ.አ. በ2026 በቻይና የአምስት ዓመት የልማት ዕቅድ ውስጥ የተካተተው ይህ ፖሊሲ፣ የአፍሪካን የኤክስፖርት ገቢ እንደሚያሳድግና የአሜሪካው የቀረጥ ነጻ ገበያ እድል (AGOA) በተቋረጠባቸው ሀገራት የሚፈጠረውን ክፍተት እንደሚሞላ ይጠበቃል። ይህ ፖሊሲ በፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ የሚመራው የቻይና መንግስት በልማት ዙሪያ ከአፍሪካ ጋር ለመስራት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።













