Loading...

የቻይናው ፕሬዝዳንት ልዩ መልእክተኛ በጅቡቲው ፕሬዝዳንት በዓለ-ሲመት ላይ መገኘታቸው ምን አንድምታ አለው?

ባለፈው ወር በተካሄደው ምርጫ  ጅቡቲን ለረጅም ጊዜ የመሩት እስማኤል ኦማር ጉሌህ ብዙም የማይታወቀውን ተቀናቃኛቸውን በከፍተኛ የድምጽ ልዩነት በማሸነፍ ለ6ኛ ጊዜ ፕሬዝዳንት ሆነዋል።

በጅቡቲ ዋና ከተማ ጅቡቲ ሲቲ ቅዳሜ እለት በተካሄደው የፕሬዝደንት ጉሌህ በዓለ ሲመት ስነስርዓት ላይ ቻይና በፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ልዩ አማካሪ ሎሳንግ ጃምካን ተወክላለች። ቻይና ከፍተኛ ባለስልጣን መላኳ ከጅቡቲ ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እንደምትፈልግ የሚያሳይ ነው። ፕሬዝዳንት ሺ፣ በልዩ መልእክተኛቸው አማካኝነት ለጁቡቲ አቻቸው “የእንኳን ደስ አለህ” እና የመልካም ምኞት መልእክት ማስተላለፋቸው፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት አሁንም ጥብቅ እንደሆነ ጠቋሚ ነው።

ቻይና እንዲህ ያሉ ከፍተኛ ባለስልጣን መላኳ ለጅቡቲ ግንኙነት ትልቅ ቦታ እንደምትሰጥ የሚያሳይ ነው። ይህ የጅቡቲ አመራርም በቻይና እንዲተማመን ያደርገዋል። ጅቡቲ ምንም እንኳን የመሬት ስፋቷና የህዝብ ቁጥሯ ትንሽ የሚባል ቢሆንም፣ ያለችበት ቀጣና በዓለም በጣም ቁልፍ በሚባለው አካባቢ ነው። በዓለም አንድ-ሶስተኛው(one-third) የሚሆነው የመርከብ ንግድ በሚካሄድበት በባብኤል ማንዴብ ሰርጥ በር ላይ ትገኛለች። ይህ ሀገሪቱ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታዋን ከፍ አድርጎታል።

በዚህ ምክንያት በጅቡቲ የጦር ሰፈር በመመስረት ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ በሚሹ ኃያላን ሀገራት ተመራጭ ሆናለች። ሊዚህ ነው አሜሪካ፣ፈረንሳይና ጃፓን የመሳሰሉ ሀገራት በቀይ ባህር ያላቸውን ተጽዕኖ ከፍ ለማድረግ በጅቡቲ የጦር ሰፈር የመሰረቱት።

ቻይና በንግድ፣ በመሰረተልማት ዝርጋታና በጸጥታ ትብብር ዘርፎች ከጅቡቲ ጋር እየሰራች ነው። በማሪታይም ንግድ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለምታደርገው ቻይና፣ በቀይ ባህር ጠረፍ ከምትገኘው ጅቡቲ ጋር ወዳጅነት መፍጠር ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ይኖረዋል። የጅቡቲ ወደቦች የቻይና እቃ በተለይም ወደ አፍሪካ ገበያ እንዲገባ እንደበር ሆነው እያገለገሉ ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪም ቻይና ከጅቡቲ ጋር ያላትን ግንኙነት ማጠናከሯ በአፍሪካ ያላት ተጽዕኖ እንዲጨምር እንዲሁም ምዕራባውያን በቀጣናው ያላቸውን የበላይነት ለመገዳደር እንድትችል ይረዳታል።

በሁለቱ ሀገራት ግንኙነት መጠንከር ሁለቱም ተጠቃሚ ይሆናሉ። እንደ ቻይና ካሉ ኃያላን ጋር ወዳጅነት መመስረት ለጅቡቲም ቀጠናዊ አስፈላጊነቷን ይጨምርላታል። ወዳጅነቱ ጅቡቲ  ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥቅሞቿን ለማስከበር የሚያስችል የመደራደሪያ አቅሟን የሚያሳድግ ነው

የቻይናና ጅቡቲ ግንኙነት ጠንካራና ዘላቂ እንዲሆን የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ወሳኝ ማና ተጫውተዋል። በጉሌህ የስልጣን ዘመን ሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በንግድ፣ በመሰረተልማት ዝርጋታና በኢንቨስትመንት በሰፊው ትብብራቸውን ቀጥሏል። ቻይና በጅቡቲ ያደረገችው ኢንቨስትመንት፣ ጅቡቲን ወደ ማሪታይምና ሎጀስቲክስ መናኸሪያነት ቀይሯታል።
በአፍሪካ የቻይና ትኩረት ጅቡቲ ብቻ አይደለችም። ቻይና ከመላው አፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን የንድግ ልውውጥና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር በዚህ ወር ተግባራዊ መሆን የጀመረውን የዜሮ ታሪፍ ፖሊሲ ማስተዋወቋ ይታወሳል። በዚህ ፖለሲ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ምርታቸውን ያለ ታሪፍ ወደ ሰፊው የቻይና ገበያ ማቅረብ ጀምረዋል

Share this article

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው