የስፔኑ ታዋቂ ክለብ ቫሌንሲያ የሴቶች ቡድን (Valencia CF Femenino B) አሰልጣኝ ፈርናንዶ ማርቲን በኢንዶኔዥያ በደረሰ አሳዛኝ የጀልባ መገልበጥ አደጋ ከሶስት የቤተሰቡ አባላት ጋር ህይወቱ ማለፉን ክለቡን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል። አሰልጣኙ እና ሶስት ልጆቹ በኢንዶኔዥያ ጉብኝት እያደረጉ በነበረበት ወቅት፣ 11 ሰዎችን አሳፍራ የነበረችው መርከብ በመስጠሟ ህይወታቸው ሊያልፍ ችሏል።
ክለቡ ቫሌንሲያ ባወጣው መግለጫ “የአሰልጣኝ ፈርናንዶ ማርቲንና የሶስት የቤተሰቡ አባላት ሞት ልባችንን በሀዘን ሰብሮታል” ሲል ገልጿል። የ44 ዓመቱ አሰልጣኝ እና ልጆቹ ከባለፈው ቅዳሜ ጀምሮ በባህር ላይ ጠፍተው የነበረ ሲሆን፣ የኢንዶኔዥያ እና የስፔን ባለስልጣናት ሲያካሂዱት የነበረው ፍለጋ እስከ ቅዳሜ ጠዋት ድረስ ቀጥሎ ነበር። የሪያል ማድሪድ ክለብም በአሰልጣኙ ሞት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገልጿል።












