የምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ጋቦን ሚዲያ ተቆጣጣሪ አካል የጥላቻ ይዘቶችና ሀሰተኛ መረጃ እየተሰራጩ እንደሚገኙ በመግለጽ በማህበራዊ ሚዲያና ዲጂታል ፕላትፎርሞች ላይ ከማክሰኞ ምሽት ጀምሮ በመላ ሀገሪቱ ላልተወሰነ ጊዜ እግድ ጥሏል።
ይህ እግድ የተጣለው በሀገሪቱ በዋናነት በመምህራን አማካኝነት የተነሳው ጸረ-መንግስት ተቃውሞ የመንግስት ተቋማትን እንቅስቃሴ በማሽመድመዱ ነው ተብሏል።
የሀገሪቱ የኮሙኒኬሽን ባለስልጣን ለእግዱ ስም የሚያጠፉና የዘለፋ ይዘት ያላቸው ይዘቶች በተደጋጋሚ መሰራጨታቸውን እንዲሁም የሀገሪቱን ደህንነት ሊያናጉ የሚችሉ የሀሰት መረጃዎች መሰራጨታቸውን እንደምክንያት ጠቅሷል።
ባለስልጣኑ እንደገለጸው በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት የሚሰራጩት ሀሰተኛ መረጃዎቾ የሀገሪቱን ተቋማት ደህንነትና ብሔራዊ ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ናቸው።
ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት “ብሔራዊና አለምአቀፋዊ ህጎችን በመጣስ ተግባራዊ አይደረግም” ያለው ባለስልጣኑ ድርጊቶቹ “ማህበራዊ ግጭቶቹን የሚያዋልዱ፣ የሀገሪቱን ተቋማት ሊያናጉ እና ሀገራዊ አንድነትን በከፍተኛ ሁኔታ ሊጎዱ” የሚችሉ ናቸው ብሏል። ተገቢ ያልሆኑ ይዘቶች ላይ ቁጥጥር ለማድረግ በኩባንያዎች በኩል ፍቃደኝነት አለመኖሩ እንዳሳዘነው የገለጸው ባለስልጣኑ ይህ የኦንላይን ተግባር በሀገር አቀፍና አለምአቀፍ ህግ ሊያስቀጣ እንደሚችል አስጠንቅቋል።
እንደ ኤፒ ዘገባ ሜታ(የፌስቡክ፣ ዋትስአፕ እና ኢንስታግራም እናት ኩባንያ) እና ቲክ ቶክ ከረቡዕ ጀምሮ በትክክል እየሰሩ አይደሉም።












