የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት ታዬ አጽቀስላሴ ቻይና ይፋ ያደረገችው የዜሮ ታሪፍ(የቀረጥ ነጻ) ፖሊሲ በኤክስፖርት የሚመራውን የአፍሪካ እድገት እንደሚያፋጥን ተናገሩ።
እኤአ በ2026 በጸደቀው የቻይና የአምስት አመት የልማት እቅድ ውስጥ የተካተተው ይህ ፖሊሲ የአፍሪካን የኤክስፖርት ገቢ እንደሚጨምርና በአሜሪካው የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና እድል(AGOA) የመጠቀሚያ ጊዜ መጠናቀቅ ምክንያት የተፈጠረውን ክፍተት እንደሚሞላ ይታመናል።
ፕሬዝደንት ታዬ በአዲስ አበባ በተካሄደው የቻይና-አፍሪካ ኢንተርፕሪኒየርሺፕ(የስራ ፈጠራ) ስብሰባ ላይ እንደተናገሩት የዜሮ ታሪፍ ፖሊሲው በአለምአቀፍ ደረጃ ያሉ የአቅርቦት ችግሮችን ስለሚቀርፉ ጠቀሜታው ከአፍሪካና ቻይና የተሻገረ ነው። ፖሊሲው የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝደንቱ አፍሪካ ሰፊውን የቻይና ገበያ እንድታገኝ እንዲሁም የቻይና ባለሀብቶች ደግሞ 1.4 ቢሊየን ህዝብ ባላት አህጉር ውስጥ ወሳኝ ቦታ እንዲይዙ የሚያስችል ነው ብለዋል።
እኤአ 2026 ለአፍሪካ-ቻይና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መታሰቢያ እንዲሆን ተደርጓል ያሉት ፕሬዝዳንቱ የሁለቱ ወገኖች ግንኙነት የብዝበዛ ባህሪ የሌለው እንደሆነም ገልጸዋል።
“ይህ አፍሪካ ስትፈልገው የነበረ አይነት ግንኘነት ነው፤ ግንኙነቱ ለብዝበዛ ሳይሆን የጋራ ራዕይ ያለው ህብረተሰብ ለመገንባት የሚጠቅም ነው።”
ፕሬዝደንት ታዬ አክለውም እንዳሉት በአሁኑ ወቅት ያለው የጂኦኢኖሚያዊ መስተጋብር ወሳኝ ማዕድናትን ለመበዝበዝ የሚደረግ ስግብግብ ፍላጎት የሚስተዋልበትና የአፍሪካን ዘላቂ ጥቅም ክብር የማይሰጥ ነው። ነገርግን የአፍሪካና የቻይና ግንኙት በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በፈጠራ ዘርፎች ላይ በጋራ ማደግን መሰረት ያደረገ ነው ብለዋል። ስራ ፈጠራ ቀዳሚ የእድገት ማነቃቂያ መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዝዳንት ታዬ አፍሪካ በተለይ የግብር ዘርፍን ከሁሉም ዘርፎች ጋር የምታስተሳስርበት አቅም እንዳለም ገልጸዋል።
ከቻይናው የዜር ታሪፍ እድል በተጨማሪ የአፍሪካን ነጻ የንግድ ቀጠና(AfCFTA) የንግድ እድሎችን ማስፋት ጠቃሚ ነው ብለዋል ፕሬዝደንቱ።
“ኢትዮጵያ በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስር መነገድ የጀመረች ሲሆን የሎጂስቲክና የማኑፋክቸሪንግ እድሎችን ለመጠቀም የኢንቨስትመንት መመሪያዎችን እየተገበረች ነው።”
የቻይና የአፍሪካ ልኡክ ኃላፊ አምባሳደር ጂያንግ ፌንግ በበኩላቸው ቻይና “የአፍሪካ ሀቀኛና አስተማማኝ አጋር ነች” ብለዋል።
የቻይና ፕሬዝደንት ሺ ጂንፒንግ ለአፍሪካ-ቻይና ትብብር ቁርጠኛ መሆናቸውን የገለጹት አምባሳደሩ ቻይና አፍሪካን በመሰረተልማት፣ በታዳሽ ኃይልና በአስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ማጎልበት እየረዳች መሆኑን ጠቅሰዋል። ይህ የቻይና ድጋፍ ለማኑፋክቸሪንግ፣ ለንግድ፣ ለመሰረተ ልማት ትስስርና ለዲጂታል ልማት ቁልፍ ትኩረት ከሚሰጠው የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 ጋር የሚጣጣም ነው ተብሏል።
አምባሳደሩ አክለው እንደገለጹት ቻይና ከአፍሪካ ጋር ለሚደረግ ትብብር ያላት ቁርጠኝነት ወጥ ነው።
አምባሳደሩ ፌንግ “ቻይና እኤአ ከግንቦት 1፣ 2026 ጀምሮ፤ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ካላት 53 የአፍሪካ ሀገራት ለሚገቡ ማንኛቸውም ምርቶች 100% የዜሮ ታሪፍ አሰራርን ተግባራዊ ታደርጋለች። ይህ ሰፊውን የቻይና ገበያ ጥራት ላላቸው የአፍሪካ ምርቶች ክፍት የሚያደርግ ትልቅ ዕድል ያደርገዋል” ብለዋል።
አምባሳደሩ እ.ኤ.አ. በ2025 በቻይና እና በአፍሪካ መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ 348 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን ጠቅሰው፣ የአፍሪካ ሀገራት ከእዚህ ዕድል ሙሉ በሙሉ እንዲጠቀሙ አሳስበዋል።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ በበኩላቸው፣ አፍሪካ ቻይና በግብርናው ዘርፍ ያመጣችውን ለውጥ አርአያ አድርጋ መስራት አለባት ብለዋል።
ቻይና እና አፍሪካ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት “ስትራቴጂካዊ አጋርነት” ሲያጣጥሙ መቆየታቸውን የጠቀሱት ሊቀመንበሩ፣ በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና በኩል የሚመጣው አህጉራዊ ውህደት ከአጀንዳ 2063 የረጅም ጊዜ ራዕይ ጋር የሚጣጣም መሆኑን ገልጸዋል።














