በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ መንታ መሆን ማለት በአንድ ቀን መወለድ፣ አንድን ማህፀን መጋራት እና ተመሳሳይ ወላጆች መኖር ማለት እንደሆነ ይታወቃል። ሆኖም ግን እንግሊዛውያኑ መንታ እህቶች ሚሼል እና ላቪኒያ ኦስቦርን ይህን የተለመደ እውነታ ገልብጠውታል። ለ49 ዓመታት ተመሳሳይ አባት እንዳላቸው አምነው የኖሩት እነዚህ እህትማማቾች በቅርቡ ባደረጉት የዲኤንኤ ምርመራ አባታቸው የተለያየ መሆኑን ደርሰውበታል።
ይህ ክስተት በሳይንስ ዓለም “Heteropaternal Superfecundation” የሚባል ሲሆን በአለም ላይ እስካሁን የታወቀው በጣት ለሚቆጠሩ ሰዎች ብቻ ነው።

ታሪኩ የጀመረው ላቪኒያ የዘር ሀረጋቸውን ለማወቅ (Ancestry DNA kit) ተጠቅማ ምርመራ ካደረገች በኋላ ነው። ውጤቱ በኢሜል ሲመጣላት ግን ያየችውን ማመን አልቻለችም። የሚሼል ስም ከጎኗ የተቀመጠው እንደ መንታ ሳይሆን እንደ ግማሽ እህት (Half-sister) ነበር።
“በሕይወቴ እርግጠኛ የሆንኩበት ብቸኛው ነገር እሷ መንታዬ መሆኗን ነበር። ድንገት ግን ያ እውነት ተቀየረ። በአንድ ሌሊት ማንነታችን ተለወጠ” ስትል ላቪኒያ ያን ድንጋጤ ታስታውሳለች።
ሳይንሱ ምን ይላል? እንዴትስ ሊሆን ይችላል?
ለመሆኑ አንዲት ሴት በአንድ ጊዜ መንታ አርግዛ አባታቸው የተለያየ ሊሆን ይችላል? መልሱ “አዎ” ነው። ይህ የሚሆነው በሚከተሉት ልዩ አጋጣሚዎች ነው፡-
- አንዲት ሴት በአንድ የወር አበባ ዑደት ውስጥ ሁለት እንቁላሎችን ካመረተች።
- እነዚህ ሁለት እንቁላሎች በአጭር ቀናት ልዩነት ውስጥ ከተለያዩ ሁለት ወንዶች በሚመጡ የዘር ፍሬዎች (Sperm) ከዳበሩ።
- በመጨረሻም ሁለቱም ፅንሶች በአንድ ማህፀን ውስጥ አብረው ካደጉ።
ይህ ክስተት በድመቶች እና በውሻዎች ላይ የተለመደ ቢሆንም በሰው ልጅ ላይ ግን እጅግ በጣም ብርቅዬ ነው። የኦስቦርን እህቶችም በእንግሊዝ ሀገር ታሪክ የመጀመሪያው ይፋዊ ተመዝጋቢ ሆነዋል።

ይህ እውነት ይፋ ከሆነ በኋላ ሁለቱም እህቶች እውነተኛ አባቶቻቸውን የመፈለግ ጉዞ ጀመሩ።
ሚሼል እውነተኛ አባቷ “አሌክስ” የተባለ ግለሰብ መሆኑን አወቀች። በሚያሳዝን ሁኔታ አባቷ ከዚህ ዓለም በሞት ቢለይም ሙሉ አዲስ ቤተሰብ እና እህትማማቾች እንዳሏት ደርሳበታለች።
ላቪኒያ አባቷ አርተር የተባሉ ግለሰብ መሆናቸውን አረጋግጣለች። ላቪኒያ አሁን ከአባቷ ጋር የጠበቀ ግንኙነት መሥርታለች። “አሁን የምገኝበትና የራሴ የምለው ቦታ ያገኘሁ ይመስለኛል” ትላለች።
“እኛ አሁንም መንታዎች ነን”
ምንም እንኳን የዲኤንኤ ውጤቱ አባታችሁ የተለያየ ነው ቢላቸውም እህትማማቾቹ ግን ትስስራቸው ከዲኤንኤ በላይ እንደሆነ ያምናሉ። “እኛ ተአምረኞች ነን” የሚሉት እህቶቹ፣ አሁንም የልደት ቀናቸውን አብረው ያከብራሉ፣ እንደ መንታም ያስባሉ።
ይህ አስገራሚ ታሪክ በሰው ልጅ ተፈጥሮ ውስጥ ምን ያህል ምስጢር ሊኖር እንደሚችል እና ሳይንስ ደግሞ እነዚያን ምስጢሮች እንዴት አውጥቶ እንደሚያሳየን ትልቅ ማሳያ ሆኗል።












