የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከቀይ ባሕርና ከብሉ ናይል (አባይ ወንዝ) ጋር በተያያዘ የሚደረግ ማንኛውም ውይይት የኢትዮጵያን ጥቅሞች ግምት ውስጥ ማስገባት እንዳለበት ገለጸ።
ይህ መግለጫ የተሰጠው ኢትዮጵያ የታጠቁ ቡድኖችን በመርዳት የምትከሳቸው ኤርትራ፣ ሱዳንና ግብፅ፣ እንዲሁም ሶማሊያ፣ ቀይ ባሕርን የማስተዳደር ሥልጣን ያላቸው የባሕሩ አዋሳኝ ሀገራት ብቻ ናቸው የሚል የጋራ የአል-አላሜይን መግለጫ ካወጡ በኋላ ነው።
ሚኒስቴሩ ሰኞ ባወጣው መግለጫ፣ ኢትዮጵያ ለናይል ወንዝ ውሃ 85 በመቶውን እንደምታበረክት እና በጂኦግራፊና በታሪክ ከቀይ ባሕር ጋር ቁርኝት እንዳላት ጠቅሷል። ቀይ ባሕርም ከኢትዮጵያ ድንበር 30 ማይል ብቻ ርቀት ላይ እንደሚገኝ ገልጿል።
በመሆኑም ሚኒስቴሩ በክልሉ የሚደረግ ማንኛውም ውይይት እነዚህን እውነታዎች ግምት ውስጥ ማስገባት እንዳለበት አስገንዝቧል።
“በጊዜ ሂደት የፖለቲካ ድንበሮች ለውጥ ቢያጋጥማቸውም፣ ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ጋር በጣም የተቆራኘች ሀገር ሆና ቀጥላለች፤ በአቅራቢያዋ ያለው ድንበርም ከባሕሩ ዳርቻ 30 ማይል ያህል ብቻ ይርቃል። ስለሆነም በክልሉ የባሕር ጉዳዮችና የደህንነት መዋቅር ላይ የሚደረግ ማንኛውም ወሳኝ ውይይት የኢትዮጵያን ሕጋዊ ጥቅሞችና ከቀይ ባሕር ጋር ያላትን ዘላቂ ግንኙነት ግምት ውስጥ ማስገባት አለበት” ሲል ሚኒስቴሩ አሳስቧል።
ሚኒስቴሩ በተጨማሪም፣ “በወኪሎች የሚደረጉ ጥቃቶች ወይም የወረራ ድርጊቶች በመሬት ላይ ያሉትን እውነታዎች አይለውጡም፤ የኢትዮጵያንም ሕጋዊ ጥቅሞች፣ ሚና እና ኃላፊነቶች አያሳንሱም” ብሏል።
ይህም በተዘዋዋሪ መልኩ ኤርትራን፣ ሱዳንን እና ግብፅን የሚያመለክት ነው።
እነዚህ የዲፕሎማሲ ግጭቶች በሰሜን ኢትዮጵያ በኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥትና በትግራይ ሕዝብ ነፃነት ግንባር (TPLF) መካከል የነበረው ግጭት እንደገና ከተቀሰቀሰ በኋላ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ደርሰዋል። ግጭቱ በአፍሪካ ቀንድና በባሕረ ሰላጤው ክልል ያሉ ሀገራትን ሊያሳትፍ ይችላል የሚል ሰፊ ስጋት ፈጥሯል።
ውጥረቱ ከተባባሰ በኋላ ኢትዮጵያ በአስመራ የሚገኘውን ኤምባሲዋን ዘግታ፣ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ደህንነት ስጋት ላይ በሚጥሉ ተግባራት ተሳትፈዋል ያለቻቸውን 10 የኤርትራ ዲፕሎማቶች በ48 ሰዓታት ውስጥ ከአዲስ አበባ እንዲወጡ ያደረገች ሲሆን አንድ የግብፅ ዲፕሎማትንም አባርራለች።
ኢትዮጵያ ያቀረበችውን ክስ በመቃወም ኤርትራ በበኩሏ ከኢትዮጵያ ጋር ያሏትን ሁሉንም ግንኙነቶች አቋረጠች፤ ግብፅም አንድ በካይሮ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሠራተኛ በ48 ሰዓታት ውስጥ ከሀገር እንዲወጣ ማድረጓ ይታወሳል።












