የኤርትራ ወታደሮች በዛሬው ዕለት በሰሜን ኢትዮጵያ በምትገኘው አዲግራት ከተማ ውስጥ ሲያልፉ መታየታቸውን ሮይተርስ ሁለት ምስክሮችን ጠቅሶ ዘግቧል።
ይህ የሆነው በአፍሪካ ቀንድ የሚገኙት ሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን በይፋ ካቋረጡ በኋላ ነው።
ኢትዮጵያ በአስመራ የሚገኘውን ኢምባሲዋን በመዝጋትና በአዲስ አበባ የነበሩ 10 የኤርትራ ዲፕሎማቶችን በማባረር ቀድማ እርምጃ የወሰደች ሲሆን፣ ኤርትራም ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የዲፕሎማሲ ግንኙነት ሙሉ በሙሉ በማቋረጥ አጸፋዊ እርምጃ መውሰዷ ይታወሳል።
በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ መፋጠጥ ውስጥ ያሉት እነዚህ ሀገራት ወደ አጠቃላይ ጦርነት እንዳይገቡ ተሰግቷል።
በሰሜን ኢትዮጵያ በህወሓትና በፌዴራል መንግሥት መካከል በድጋሚ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ፣ የኤርትራ ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ ግዛት መግባታቸው ሲዘገብ ይህ የመጀመሪያው ነው።
የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የሆኑት የማነ ገብረመስቀል ግን የኤርትራ ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ገብተዋል መባሉን አስተባብለዋል። ሚኒስትሩ አክለውም ኢትዮጵያ ይህን ክስ የምታቀርበው በኤርትራ ላይ ለመክፈት ያሰበችውን ጦርነት ምክንያታዊ ለማድረግ ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ኤርትራ ከሱዳንና ከግብጽ ጋር በመሆን ህወሓትን ጨምሮ በሀገር ውስጥ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ቡድኖችን እየረዳች ነው የሚል ጠንካራ ክስ እያቀረበ ይገኛል። ኤርትራ ይህን ክስ ማስተባበሏን ትቀጥላለች።
በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለው ወቅታዊ ውጥረት ያሳሰባቸው አሜሪካ፣ የአፍሪካ ህብረትና የአውሮፓ ህብረት፣ ውጥረቱ የአፍሪካ ቀንድን ከማተራመሱ በፊት በውይይትና በድርድር እንዲፈታ አሳስበዋል።












