በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተፈጠረውን ከፍተኛ ፍጥጫ ተከትሎ አሜሪካ በኤርትራ ለሚኖሩ ዜጎቿ የጥንቃቄ መልእክት አስተላልፋለች።
በአስመራ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ዛሬ ባወጣው አጭር መግለጫ በሰሜን ኢትዮጵያ በኤርትራ ድንበር አቅራቢያ ጦርነት እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሶ፤ “የአሜሪካ ዜጎች የጉዞ ክልከላዎች፣ ፈንጅዎች ተገቢ ያልሆነ እስርና ውሱን የኤምባሲ እርዳታ” ሊኖር ስለሚችል ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስቧል።
ኤርትራ ጥምር ዜግነት (Dual citizenship) እንደማትቀበል የገለጸው መግለጫው፤ አሜሪካውያን እንደ ኤርትራዊ ታይተው ግብር ሊከፍሉ ወይም ለብሔራዊ ውትድርና ሊመለመሉ እንደሚችሉ ገልጿል።
ኤምባሲው አክሎም የኤምባሲው ባልደረቦች ከማዕከላዊ አስመራ 25 ኪሎሜትር በላይ ለሚጓዙ ዜጎች ለመርዳት እንደሚቸገር ገልጿል።
ከሁለት ሳምንት በፊት በፌደራል መንግስትና በህወሓት መካከል የትጥቅ ግጭት እንደገና ማገርሸቱን ተከትሎ፤ በኢትዮጵያና ህወሓትን ጨምሮ የሀገር ውስጥ ታጣቂዎችን ትረዳለች የሚል ክስ በሚቀርብባት ኤርትራ መካከል ያለው ፍጥጫ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል።
የኤርትራ መንግስት በኢትዮጵያ መንግስት የሚቀርብበትን ክስ በተደጋጋሚ አስተባብሏል።
ከቀናት በፊት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ቲሞቲዎስ፣ የኤርትራ ጦር ድንበር ጥሶ መግባቱን ጠቅሰው በአስቸኳይ የማይወጣ ከሆነ ኢትዮጵያ ራሷን እንደምትከላከል አስጠንቅቀዋል። የኤርትራ መንግስት ግን ኢትዮጵያ ይህንን ክስ የምታቀርበው ያቀደችውን ወረራ ምክንያታዊ ለማድረግ ነው በሚል ውድቅ አድርጎታል።












