የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ዛሬ ባወጣው መግለጫ “የህወሓት አመራር ለአራተኛ ጊዜ የጀመረውን ጦርነት” መሸነፉን ገልጾ፣ የትግራይ ክልል ህዝብ በፌደሬሽን ምክርቤት የሚገባውን ውክልና አግኝቶ ፊቱን ወደ ልማት እንዲያዞር ለማስቻል ነው የባለአደራ አስተዳደር ማቋቋም ያስፈለገው ብሏል።
መግለጫው ባለአደራው አስተዳደር የሰላምና የመረጋጋት ሁኔታን ማስፈን፣ የተበላሹ የመንግሥት መዋቅሮችንና መሠረተ ልማቶችን መልሶ ማቋቋም፣ የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው መመለስና የተቋረጡ ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ማስቀጠል ዋና ተግባራቱ ይሆናሉ።
አስተዳደሩ በ6 ወራት ውስጥ ነፃና ግልጽ ምርጫ እንዲካሄድ ሁኔታዎችን የማመቻቸትና የክልሉን የጸጥታ መዋቅር እንደገና የማደራጀት ኃላፊነትም ተሰጥቶታል። አቶ አሰፋ አብርሃ ሐጎስ፣ ዶክተር ቴዎድሮስ አረጋይ ወልደሥላሴ፣ ብርጋዴር ጄኔራል ገብረ እግዚአብሔር በየነ ኃይሉ እና አቶ ረዳኢ ኃለፎም ወልደሥላሴ የባለአደራ አስተዳደሩ ዋና ስራ አስፈጻሚዎች ሆነው ተሹመዋል። ዶክተር ሽሻይ አማረ ደግሞ የመቐለ ከተማ ከንቲባ ሆነው ተሹመዋል።
አዲሱ አስተዳደር በፌዴራል መንግሥት መመሪያና ክትትል ሥር እንደሚሠራ፣ በክልሉ የተመረጠ መንግሥት እስኪቋቋም ድረስም የዕለት ተዕለት አስተዳደራዊ አገልግሎቶችንና ለምርጫ የሚያስፈልጉ ዝግጅቶችን እንደሚያከናውን መግለጫው ያትታል።













