Loading...

ባህል በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ታጅቦ የሚቀርብበት የ2026ቱ የቻይና አዲስ አመት ትዕይንት

ከፊፋ የአለም ዋንጫ ቀጥሎ በአለም በሁለተኛ ደረጃ የሚታየው የቴሌቪዥን ትዕይንት(ጋላ) ፌብሩወሪ 16፣2026 ከምሸቱ ሁለት ሰአት ይጀምራል። ሚሊዮኖች ለ4.5 ሰአታት ከመቀመጫቸው እንዳይነሱ የሚያደርጋቸው ምን ሊሆን ይችላል? መልሱ በቻይና ማዕከላዊ ቴሌቪዥን(ሲሲቲቪ) የሚተላለፈው የቻይና የአዲስ አመት ትዕይንት ነው የሚል ነው።
ትዕይንቱ ዘመናዊ የሚዲያ ቴክኖሎጂዎችንና ባህላዊ ክንውኖችን የሚያካትት በቻይና አዲስ አመት ዋዜማ በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭትና በኦንላይን ሚዲያ ፕላትፎሞች(መድረኮች) የሚተላለፍ መዝናኛ ነው።

በቻይና ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ቻይናውያን ቤተሰቦች ለማየት በጉጉት የሚጠብቁት ነው። ትዕይንቱ ለመጀመሪያ ጊዜ መተላለፍ ከጀመረበት ከ1983 ጀምሮ በማሰራጫ ቴክኖሎጂዎች፣ በቴክኒክና በይዘት ደረጃ ሲታይ ጉልህ ለውጥ አስተናግዷል። የ2025ቱን ትዕይንት በሁሉም የሚዲያ አማራጫች (በተለይ በቴሌቪዥንና ኦላይን) ባልተጠበቀ ሁኔታ 16.8 ሚሊዮን ተመልካቾች እንዳዩትና ይህም ከ2024ቱ ጋር ሲነጻጸር የ 18.31 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን የቻይና ሚዲያ ግሩፕ ሪፖርት አድርጓል።

ትዕይንቱ በ1983 ለመጀመሪያ ጊዜ ሲተላለፍ ተመልካቾች ትዕይንቱን ያዩት በአናሎግ ቴሌቪዥን ሲሆን የምስል ጥራቱም በአሁኑ ወቅት ካለው ጋር ሲነጻጸሩ ዝቅተኛ ነበር፤ ይዘቱም ውስን እንደነበር ይታወቃል።ከዚህ በተጨማሪ የቻይና ቴክኖሎጂ ያልዘመነ እንዲሁም አብዛኛው የቻይና ህዝብ ኢኮኖሚውን ለማሻሻል ሲታገል የነበረ በመሆኑ ለባህላዊ መድረኮች የሚሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ ነበር። የመጀመሪያዎቹ የአዲስ አመት ትዕይንቶች ሁልጊዜ የሚቀርቡባቸው የአንበሳ ዳንስና የድራጎን ዳንስ የመሳሰሉ ባህላዊ ክንውኖች፣ ትሪኮችና ሌሎች የአክሮባቲክስ አይነቶች ነበሩ።

ይህ ትዕይንት እንደሌሎች ለረጅም ጊዜ እንደቆዩ ባህሎች ሁሉ በዋናነት በወጣቶች የሚከበርበት ሁኔታ “አሮጌ” ወይም ፋሽን ያለፈበት ነው የሚል ተቃውሞ አጋጥሞታል። ወጣቶቹ አከባበሩ መዘመን አለበት ብለው ይሞግታሉ። የቻይና የኢኮኖሚ እድገትና የቴክኖሎጂ መዘመን ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ሰጥቷል። ይህ የፈረሶቹ አመት አከባበር የቴክኖሎጂ ሙሉ ኃይል የሚታይበት ይሆናል። የ5ጂ፣ የ4ጂ፣ የ8ኬ መተግበሪያዎችን በማጣመር እንዲሁም ቨርቹዋል ሪያሊቲ ቴክኒኮችን በመጠቀም ተመልካቾች ለየት ያለ ልምድ እንዲያገኙ የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል።

የዚህ አመቱ ትዕይንት መድረክ ክብረወሰን የሰበረ 1462 የመብረት ስርአቶች ያሉት ሲሆን ማብሪያ ማጥፊያዎቹ፣ የብርሃን መጠኑ፣ ቀለሞቹና እንቅስቃሴዎች በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ቁጥጥር ይደረግባቸዋል።

የተጨመረ እውነታ(አውግመንትድ ሪያሊቲ)፣ የተስፋፋ እውነት (ኤክስቴንድድ ሪያሊቲ) እና አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ምናባዊውን አለምና ትክክለኛውን እውነታ ቀላቅሎ መሳጭ መድረክ ለማዘጋጀት ጥቅም ላይ ይውላሉ።

ቀደም ባሉት ትዕይንቶች ላይ ሚቀርቡት ይዘቶች እንዳሉ ሆነው፣ ዘፈን፣ ክሮስ-ቶክ፣ ዳንስ፣ ስኬቺንግ፣ ማጅክ፣ የቀልድ ትዕይንቶች፣ አክሮባቲክስና የመሳሰሉ ክንውኖች እና በከፍተኛ ቴክኖሎጂ የሚቀርበው የቻይና ኦፔራ የዘንድሮው ትዕይንት አካል ናቸው።

ምንምእንኳን ብዙ ለውጦች ቢኖሩም ሳይለወጥ የቀጠለ አንድ ነገር አለ። ይህም ትዕይንቱ ቻይናውያን ቤተሰቦች በአንድ ቦታ ተሰብስበው ቴሌቪዥን እንዲያዩ ብቻ ሳይሆን ከባህላቸው ጋር እንዲተሳሰሩ ወሳኝ ሚና መጫወቱ ነው። የሲሲቲቪ የአዲስ አመት ትዕይንት ቀጥታ ስርጭት በዓሉን እያወሩ፣ እየሳቁና እየተዝናኑ ለሚያከብሩ ቤተሰቦች ተጨማሪ ምቾት በመፍጠር ወሳኝ ሚና ይጫወታል።

ከ30 አመታት በላይ ያስቆጠረው ይህ ትዕይንት የቻይናን የብሮድካስት ኢንዱስትሪ ቴክኖሎጂ መዘመን ሲያሳይ የቆየ ሲሆን ዛሬም የቻይናን ባህል ለአለም ህዝብ ለማሳየት ከፍተኛ ሚና ያለው መድረክ ሆኖ ቀጥሏል።

Share this article

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው