Loading...

ኢትዮጵያ እድሏን ተነጥቃለች? ወይስ ግዜው አልረፈደም?የሶማሌላንድ እውቅና ለኢትዮጵያ ያለው ትርጉም

የሶማሌላንድ እውቅና ማግኘት የኢትዮጵያ ወደብ ባለቤትነት እና ቀጠናዊ አቅምን የማጠናከር ፍላጎት ላይ አዲስ ክርክሮችን አስነስቷል። አንዳንድተንታኞች የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ትብብር የንግድ እና የሃይል ትስስርን ይፈጥራል ይላሉ፣ ሶማሊያ በተቃራኒው የድንበር ሉዓላዊነቷን እንደሚነካ በመጥቀስ ትቃወመዋለች። ኢትዮጵያ ግንኙነቷን እንደገና ለማደስ ያላት አማራጭ አሁንም አጠያያቂነቱ ቀጥሏል።

“ኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅሟን ማስቀደም አለባት” ዘመዴነህ ንጋቱ

ኢትዮጵያዊው ኢኮኖሚስት እና አለም አቀፍ ተንታኝ ዘመዴነህ ንጋቱ ከቢቢሲ አፍሪካ ጋር ባደረጉት ቆይታ የሶማሊላንድ አገርነት እውቅና ለኢትዮጵያ የሚኖረው ትርጉም “አዎንታዊ” ነው ይላሉ። እውቅናው ኢትዮጵያ ተፈራርማ የነበረውን የ50 አመት የወደብ ባለቤትነት ስምምነት ወደ እውነታ የሚቀይር እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ዘመዴነህ፥ ኢትዮጵያ ከሰሃራ በረሃ በታች ካሉ አገራት በምጣኔ ሃብቷ ናይጄሪያ እና ደቡብ አፍሪካን ተከትላ ሶስተኛ ላይ የተቀመጠች መሆኗን በማንሳት ይህ እውነታ አገሪቱ ወደቦችን እንድታበዛ የሚያስገድድ እንደሆነ ይገልጻሉ። በተጨማሪም አገሪቱ እያስፋፋች የምትገኘውን የኤሌክትሪክ ሃይል ከአገር ውስጥ እድገት ባሻገር ለሰፊው የምስራቅ አፍሪካ በማጋራት ለጋራ እድገት የምታውለው መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ተፈራርማ የነበረው የ50 አመታት የወደብ ኪራይ ኢትዮጵያን የወደብ ባለቤት የሚያደርግ እድል ፈጥሮ የነበረ ቢሆንም ፥ ስምምነቱን ሶማሊያ የግዛት ሉዓላዊነቷን የሚጥስ እንደሆነ በመግለጽ ውድቅ አድርጋው እንደነበር ይታወሳል። በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መሃል የሰፈነው ውጥረትም በቱርክ አማላጅነት በአንካራ በተደረሰ ስምምነት ሊረግብ ችሏል።

እንደ ዘመዴነህ ንጋቱ ምልከታ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር እንደገና ቅርርቧን ለማደስ ብትሞክር በሶማሊያ እንደ ዲፕሎማሲያዊ ክህደት ሊቆጠር አይገባም። ይህንም ከሰፊው አህጉራዊ የግንኙነት ራእዮች አንጻር በመመልከት መፍታት እንደሚቻል ያስረዳሉ።

እስራዔል ለሶማሊላንድ አገርነት እውቅና መስጠቷን ተከትሎ፥ ከዚህ ቀደም ውጥረትን ለማርገብ የተደረጉ ስምምነቶችን ዋጋ በማሳነስ ኢትዮጵያ በጥያቄዋ ጸንታ መግፋት ነበረባት የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች ይደመጣሉ። በሌላ በኩል አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ደርሳ የነበረውን ስምምነት ማደስ አለባት የሚሉ አስተያየቶች ከየአቅጣጫው እየተሰጡ ይገኛሉ።

Share this article

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው