Loading...

ኢትዮጵያ የግብፅን ” የቅኝ ግዛት ስርዓት አስተሳሰብ” አጥብቃ ነቀፈች

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በታህሳስ 3 ቀን 2025 የግብፅ ባለስልጣናት በቅርቡ ያቀረቡትን ንግግር አስመልክቶ ጠንካራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። መግለጫው ግብፅን “ከቅኝ ግዛት ዘመን አስተሳሰብ ጋር የሙጥኝ በማለት፣” ጊዜ ያለፈባቸውን ስምምነቶች መጥቀስ እና የአባይ ወንዝ ውሃ የታችኛው ተፋሰስ አገራት ንብረት ብቻ እንደሆነ መቁጠሯን ቀጥላለች ሲል ነቅፏል። ኢትዮጵያ እንደሌሎች የተፋሰሱ ሀገራት ከግብፅ ፍቃድ ሳትጠይቅ በድንበሯ ውስጥ የሚገኝ ውሃዋን የመጠቀም ሉዓላዊ መብት እንዳላት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው አስታውቋል ።

ግብጽ በአፍሪካ ቀንድ ላይ “የማተራመስ” ዘመቻዋን የቀጠለች መሆኑን መግለጫው በእጽንዖት ይገልጻል። መግለጫው፣ የግብፅ ባለስልጣናት ድርድሮችን ሙሉ በሙሉ ውድቅ በማድረግ እና ማስፈራሪያዎችን በመሰንዘር፥ ምዕናብ የጎደለው እና የአመራር ውድቀት የሚያሳይ መንገድን መርጣለች ይላል። ኢትዮጵያ የአባይ ውሃ አጠቃቀም ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ በሆነ የአለም አቀፍ የውሃ ህግ መገዛት እንዳለበት እና አገሪቱ መብቷን ለቅኝ ግዛት ስምምነቶች አሳልፋ እንደማትሰጥ ጨምሮ ገልጿል።

በተጨማሪ፣ ኢትዮጵያ የናይል ገባር ወንዞችን ጉዳይ ከሀገር ውስጥ ፖሊሲ አንጻር ብቻ ሳይሆን እና የአፍሪካውያን የአብሮነት እና እራስን የመቻል አቋም አንድ አካል አድርጋ እንደምትመለከተው መግለጫው ያስረዳል። መግለጫው፥ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያሉ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን አድገት ፍላጎት እና የአፍሪካን እራስ የመቻል ተምሳሌት አድርጋ እንደምትቆጥረው ይጠቅሳል። ሚኒስቴሩ በአባይ ወንዝ ላይ የሚደረግ ማንኛውም ስምምነት በፍትሃዊነት እና በመልካም ጉርብትና ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ጠይቋል ።

በቅርቡ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብደላቲ የካይሮን አቋም በድጋሚ በገለጹበት አስተያየታቸው፥ “የአባይ ወንዝ ድርድር ከአስር አመታት በላይ ፍሬ አልባ ንግግሮች በኋላ በድርድር የማይፈታበት ደረጃ ላይ ደርሷል።” ሲሉ የገለጹ ሲሆን፥ ግብፅ የናይል ውሃ ድርሻዋ ለድርድር የማይቀርብ የህልውና ጉዳይ አድርጋ እንደምትመለከተው አፅንዖት ሰጥተው ተናግረው ነበር። ሚኒስትሩ፥ “ግብጽ፥ በአለም አቀፍ ህግ መሰረት የውሃ ፍላጎቷን የመጠበቅ መብቷ የተጠበቀ ነው” በማለት ሌሎች አማራጮችን እንደሚመለከቱ አስታውቀዋል።

የመግለጫ ልውውጡ፣ በአዲስ አበባ እና በካይሮ መካከል የአባይ ውሃ አጠቃቀም መርሆዎች ላይ ያለው ክፍተት ምን ያህል እንደሰፋ ያሳያል። መደበኛ ውይይቶች ባሉበት በቆሙበት ሰዓት የቃላት ልውውጦች እየጠነከሩ የቀጠሉ ሲሆን፣ ይህም ቀጣናዊ ውጥረቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያየለ መሄዱን ያሳያል።

Share this article

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው