የሰይፍ አል ኢስላም ህይወት ከብዙ በጥቂቱ ምን ይመስላል? ገዳዮቹስ እነማን ናቸው?
ባለፈው ማክሰኞ በመኖሪያ ቤቱ ተገድሎ የተገኘው የቀድሞው የሊቢያ አምባገነን ሙዓመር ጋዳፊ ልጅ ሰይፍ አሊ ኢስላም ባኒ ዋሊድ በተባለች የሊቢያ ትንሽ ከተማ ቀብሩ ተፈጽሟል። በሺህዎች የሚቆጠሩ ሊቢያውያን ደጋፊዎቹም በቀብሩ ላይ ተገኝተዋል።
ሰይፍ አል ኢስላም በቀጣዮቹ ሁለት ወራት ውስጥ የሚካሄደው የሊቢያ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ላይ የማሸነፍ እድል ስለነበረው በተቃዋሚዎቹ ሸፍጥ እንደተገደለ በመግለጽ ክስ ያሰሙ ደጋፊዎቹ ነበሩ።
የጋዳፊ ሁለተኛ ልጅ የነበረው ሴፍ አል ኢስላም የአባቱ ስልጣን ተረካቢ እንደሚሆን የሚጠበቀው ልጃቸው ነበር። ጋዳፊ እ.ኤ.አ. በ2011 በኔቶ ጦር መሪነት በሚደገፍ አመጽ ከስልጣን ከወረዱ እና በአማጺዎች ከተገደሉ በሗላ ተራ መንገደኛ መስሎ ወደ ኒጀር ለማምለጥ ሲሞክር በሚሊሻዎች ተይዞ ለአመታት በእስር ቆይቷል።
በአለም አቀፉ ፍርድ ቤት ሰይፍ አል ኢስላም ላይ በጦር ወንጀለኝነት ክስ ከፍቶበት ተላልፎ እንዲሰጠው ሲጠይቅ ከቆየ በሗላ ከሊቢያ ግዜያዊ አስተዳደር ጋር በተደረገ ድርድር የወንጀል ፍርዱ በሊቢያ ህግ ስር እንዲፈጸም ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር።
በመጀመሪያ የሊቢያ ግዜያዊ አስተዳደር የሞት ፍርድ አስተላልፎበት የነበረ ቢሆንም ከግዜ በሗላ ሰይፍ አል ኢስላም ምህረትን አግኝቶ ከእስር በነጻ ተለቋል። ከእስር ነጻ ከወጣ በሗላ ዚታን በምትባል ከተማ አከባቢ ውስጥ ይኖር ነበር።
የ53ቱ ሰይፍ አል ኢስላም በመንግስታቱ ድርጅት ድጋፍ በተቀመጠው አስተዳደር ስር ሊካሄድ የታቀደው የመጀመሪያው የሊቢያ ነጻ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ ሲጠባበቅ ነበር። በሊቢያ ያለው ሰላም ከፈቀደ ምርጫው ከሁለት ወራት በሗላ ማለትም እ.ኤ.አ. ኤፕሪል 2026 ላይ ሊካሄድ ቀጠሮ ተይዞለታል።
ከዚህ አስቀድሞ እ.ኤ.አ. በ2021 ሊከሄድ ተሞክሮ የነበረው ምርጫ ላይ ለእጩነት አመልክቶ በሊቢያ የምርጫ ኮሚሽን ጥያቄው ውድቅ ተደርጎበት ነበር። ሆኖም በይግባኝ የእጩነት ቦታውን ዳግም ሲያገኝ በጋዳፊ ስልጣን ዘመን ተበዳይ የነበሩ ተቃውሚዎች ውሳኔው አላስደሰታቸውም። በሊቢያ በቀጠለው አለመረጋጋት ምክንያትም ምርጫው ሳይካሄድ ቀርቷል።
ሰይፍ አል ኢስላም ከአባቱ በተሻለ ሁኔታ ሊቢያን ከምዕራቡ አለም ጋር ለማቀራረብ በአደረጋቸው አስተዋጽዖዎቹ፥ ህገ መንግስታዊ ስርዓትን በሊቢያ እውን ለማድረግ በነበረው ፍቃደኛነት በምዕራቡ አለም መንግስታት እና በሊቢያ መሃል በተደረጉ የኒውክሊየር ድርድሮች ላይ በነበረው ትልቅ ሚና እንዲሁም በበርካታ ዲፕሎማሲያዊ ተሳትፈዎቹ ይታወቃል። ነገር ግን ይፋዊ የመንግስት ስልጣን አልያዘም ነበር።












