ሶማሊያ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ስትከተለው የነበረውንና በፕሬዝዳንቱ እና በጠቅላይ ሚኒስትሩ መካከል ስልጣን ተከፋፍሎ የሚገኝበትን “የፓርላማ ሥርዓት” በይፋ በመተው ወደ “ፕሬዝዳንታዊ ሥርዓት” ለመሸጋገር ወስናለች። ይህ ለውጥ በሀገሪቱ ከፍተኛ የሥልጣን እርከን ላይ ያለውን ሚዛን ሙሉ በሙሉ የሚቀይር ነው።
የፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ አስተዳደር ለውጡን አስፈላጊ ያደረጉትን ምክንያቶች መካከል
- ባለፉት ዓመታት በሶማሊያ ፕሬዝዳንቶች እና በጠቅላይ ሚኒስትሮቻቸው መካከል የሚፈጠረው አለመግባባት መንግሥትን ለወራት ስራ ያቆም ነበር። ስልጣኑን በአንድ ፕሬዝዳንት ስር ማጠቃለል ይህንን “የሁለት ራስ” ችግር ይፈታዋል ተብሏል።
- ሀገሪቱ ከአል-ሸባብ ጋር በከባድ ጦርነት ላይ ባለችበት ወቅት ፈጣንና ወጥ የሆነ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ውሳኔዎችን ለማሳለፍ ፕሬዝዳንታዊ ሥርዓቱ የተሻለ እንደሆነ ይታመናል።
የሥልጣን አወቃቀሩ ምን ይመስላል?
በአዲሱ ማሻሻያ መሠረት ፕሬዝዳንቱ የሀገርም የመንግሥትም መሪ ይሆናሉ። የሚሾሙት ግለሰብም “ጠቅላይ ሚኒስትር” ተብለው ቢጠሩም እንደ ቀድሞው ራሱን የቻለ ስልጣን ሳይኖራቸው የፕሬዝዳንቱ ረዳት ሆነው ያገለግላሉ።
ቀደም ሲል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፓርላማው ተጠያቂ የነበሩ ሲሆን አሁን ግን በቀጥታ ለፕሬዝዳንቱ ተጠያቂ ይሆናሉ። ይህም ፕሬዝዳንቱ ካቢኔያቸውን ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት እንዲመሩ ያስችላቸዋል።
ተቃዋሚዎች ይህ ለውጥ ሶማሊያን ወደ አደገኛ አቅጣጫ ሊወስዳት ይችላል ይላሉ።
ስልጣን በአንድ ግለሰብ እጅ መከማቸቱ ተቋማዊ አሰራርን በማዳከም አምባገነንነትን ሊወልድ ይችላል የሚል ስጋት አለ።
ክልሎች (እንደ ፑንትላንድ) ይህ ለውጥ የማዕከላዊ መንግሥቱን ጡንቻ በማፈርጠም የክልሎችን የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ይጋፋል በሚል በከፍተኛ ሁኔታ እየተቃወሙት ይገኛሉ።












