የቀድሞዋ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዥ አማካኝነት በምዕራብ አፍሪካና ሳህል የሰላም ጽሕፈት ቤት (UNOWAS) ከፍተኛ ገለልተኛ ስትራቴጂያዊ ገምጋሚ ሆነው ተሾሙ።
የተመድ ምዕራብ አፍሪካና ሳህል ቢሮ (UNOWAS) በቀጣናው ለሚከሰቱ ቀውሶች ፈጣን ምላሽ ከመስጠት አኳያ ያሉበትን የአሠራር ክፍተቶች እና አጠቃላይ ተቋማዊ ብቃቱን መገምገም የሣህለወርቅ ዘውዴ ዋና ተልዕኮ ይሆናል።
ምዕራብ አፍሪካ እና የሳህል ቀጠና በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ የጸጥታ መቃወስ በሽብርተኝነት ስጋት እና በፖለቲካዊ አለመረጋጋት ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ ይህ ገለልተኛ ግምገማ ለተመድ ቀጣይ ስትራቴጂ ወሳኝ እንደሆነ ተገልጿል።
የቀድሞዋ ፕሬዚዳንት ኃላፊነታቸውን በዚህኛው ወር (ጁን) ማብቂያ ላይ በይፋ የሚረከቡ ሲሆን፣ ሥራቸውን በኒውዮርክ በሚገኘው የተመድ ዋና መሥሪያ ቤት ከተመድ የጸጥታው ምክር ቤት አባላት ጋር በሚያደርጉት ምክክር ይጀምራሉ። በመቀጠልም የቢሮው መቀመጫ ወደሆነችው ዳካር፣ ሴኔጋል በማምራት ስትራቴጂያዊ ግምገማውን በይፋ ያስጀምራሉ።
ተመድ ባወጣው መረጃ መሠረት ሣህለወርቅ ዘውዴ ለዚህ ወሳኝ ኃላፊነት የተመረጡት በቀጠናው ባላቸው የረጅም ዓመታት ሰፊ ዲፕሎማሲያዊ ልምድ እና እውቅና ነው። ፕሬዚዳንት ከመሆናቸው በፊት መቀመጫቸውን ሴኔጋል በማድረግ ለማሊ፣ ጊኒ እና ኬፕ ቨርዴ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው ማገልገላቸው የምዕራብ አፍሪካን ጂኦ-ፖለቲካዊ ፈተናዎች በጥልቀት እንዲረዱ ትልቅ አቅም ሆኗቸዋል።












