ኢትዮጵያና ኬንያ በተለይም በአፍሪካ ቀንድ በተጽዕኖ አንዳቸው ሌላኛቸውን ለመብለጥ ለረጅም ጊዜ ሲፎካከሩ ቆይተዋል። ሁለቱም ሀገራት በዲፕሎማሲ፣ በስትራቴጂያዊ አጋርነቶች፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችንና ጉባኤዎችን በማስተናገድ እንዲሁም በቀጠናዊ ግጭቶች የሽምግልና ሚና በመጫወት ተጽዕኗቸውን ለማጠናከር ተግተዋል።
ፉክክራቸው መልካም ተዕጽኖ በመፍጠር(Soft power) ላይ ያተኮረ ነው።ሀገራቱ ለብዙ ዓመታት የቆየ ወዳጅነት ያላቸው ሲሆን፣ በደኅንነት ጉዳዮችም ይተባበራሉ። በጋራ ድንበራቸው አካባቢ የሚንቀሳቀሱ አማፂ ቡድኖችን ለመዋጋት የወታደራዊ ትብብር ስምምነቶች አሏቸው።
በታሪክ ኢትዮጵያ በቀጣናው ብሎም በአፍሪካ አህጉር ተጽዕኖዋ ከፍ ያለ ነበር። ይህም በዋናነት የአፍሪካ ህብረት ዋና መሥሪያ ቤት መቀመጫና ከቀዳሚዎቹ የተባበሩት መንግስታት ድርጀት መሥራች አባላት አንዷ በመሆኗ የመጣ ነው። ኢትዮጵያ እነዚህን ታሪካዊ እውነታዎች ገጽታዋን ለመገንባትና ተጽእኖዋን ለመጨመር ተጠቅማበታለች።
በቅርብ ዓመታት ግን ኬንያ በቀጣናው ያላትን ሚና ለማሳደግ በትጋት እየሠራች ይመስላል። ለዚህ አንዱ ማሳያ የተባበሩት መንግስታት ድርጀት የናይሮቢ ቢሮውን በ400 ሚሊዮን ዶላር ወጭ ለማስፋፋት ግንባታ ፕሮጀክት መጀመሩ ነው። ፕሮጀክቱን ያስጀመሩት የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ እና የኬንያ ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ ናቸው።የኬንያ መንግስት እነዚህን ሁነቶች የሀገሪቱ ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ መጨመር ማሳያ አድርጎ ሲያቀርባቸው ይስተዋላል። በተጨማሪም ኬንያ ወሳኝ የሆኑ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች በማስተናገድ በተለይ ከምዕራባውያን ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት እያጠናከረች ነው።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ከምዕራባውያን ጋር ያላትን ግንኙነት አስጠብቃ ወደ ብሪክስ (BRICS) በመቀላቀል የተለያዩ የዲፕሎማሲ አጋርነቶችን እያሰፋች ነው። ይሁን እንጂ ኬንያ ከአሜሪካ እና ከምዕራባውያን አጋሮቿ ጋር ያላትን ግንኙነት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል።
ሁለቱም ሀገራት በአፍሪካ ቀንድ ቀዳሚ ኃይል ለመሆን እየተፎካከሩ መሆናቸው ግልጽ ነው። ሆኖም በአሁኑ ወቅት የትኛዋ ሀገር በዚህ ፉክክር ቀዳሚ እንደሆነች ግልጽ ውሳኔ መስጠት አዳጋች ነው።
የዲፕሎማሲ ተፅዕኖ ብዙ ጊዜ በዓለም አቀፍ ተደማጭነትና በፖለቲካዊ ግንኙነቶች ይለካል። በጀትና የዕዳ ጫና እና የመሳሰሉ ኢኮኖሚያዊ መለኪያዎች ግን የአንድ ሀገርን መሠረታዊ ጥንካሬ ለመገምገም የበለጠ ተጨባጭና ትክክለኛ መለኪያ ሊሆኑ ይችላሉ።

የሁለቱ ሀገራት የኢኮኖሚ ሁኔታ በእነዚህ የማክሮኢኮኖሚ መለኪያዎች ሲገመገም ምን መልክ አለው?
ብሔራዊ በጀቶች
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የበጀት ልዩነት ከፍተኛ ነው። የኬንያ የ2026/27 በጀት 37 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን ኢትዮጵያ ከበጀተችው 14.5 ቢሊዮን ዶላር ጋር ሲነጻጸር ወደ ሦስት እጥፍ ገደማ ይሆናል።
እነዚህ አሃዞች የኬንያ የመንግስት የወጪ አቅም ከኢትዮጵያ በእጅጉ የላቀ መሆኑን ያሳያሉ። ይህ ልዩነት በነፍስ ወከፍ ገቢም ይታያል። የኬንያ የነፍስ ወከፍ ገቢ 1,500 ዶላር ገደማ ሲሆን የኢትዮጵያ ደግሞ 500 ዶላር ገደማ ነው።
ምንም እንኳን ኢትዮጵያ አነስተኛ ኢኮኖሚ ቢኖራትም የእድገት መጠኗ ፈጣን የሚባል እንደሆነ ትንበያዎች ያሳያሉ። በቅርቡ የወጡ የኢኮኖሚ እድገት ትንበያ አሀዞች መሰረት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ 10.2 በመቶ እንደሚያድግ ሲተነብዩ የኬንያ ደግሞ 4.8 በመቶ እንደሚያድግ ጠቅሰዋል።
የዕዳ ጫና
ዕዳ በአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ አፈጻጸም ላይ ትልቅ ተፅዕኖ የሚያሳድር የማክሮ ኢኮኖሚ መለኪያ ነው። ምንም እንኳን ኬንያ ከኢትዮጵያ የላቀ በጀት ቢኖራትም የዕዳ ጫናዋ ከፍተኛ ነው።
እ.ኤ.አ. በመጋቢት 2026 የኬንያ የመንግስት ዕዳ 99 ቢሊዮን ዶላር የደረሰ ሲሆን ይህም ከሀገሪቱ ጠቅላላ ምርት 70 በመቶ ገደማ ይሸፍናል። በመሆኑም ከሀገሪቱ በጀት ቀላል የማይባል ገንዘብ ለዕዳ ክፍያ ይውላል ማለት ነው።
ኢትዮጵያም የዕዳ ችግሮች ቢኖርባትም የዕዳ ጫናዋ ከኬንያ ያነሰ ነው። አለምአቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) መረጃ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ የመንግስት ዕዳ በ2025 አጋማሽ የአጠቃላይ ሀገር ውስጥ ገቢዋ (GDP) 50 በመቶ ገደማ ነበር።
ዓለምአቀፍ የረሃብ መጠን ጠቆሚ
ሀገራትን በምግብ እጥረት፣ በሕፃናት መቀንጨር (stunting)፣ በሕፃናት መቅጠን (wasting) እና በሕፃናት ሞት(Child morality ) መጠን የሚለካው ዓለምአቀፍ የረሃብ መጠን ጠቋሚ(Global Hunger Index) መሰረት ኬንያ ከኢትዮጵያ ከፍ ያለ የረሃብ ደረጃ ላይ ነች። የኬንያ የረሃብ ጠቆሚ ውጤት 25 ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ደግሞ 24.4 ነው። በተመሳሳይ በምግብ እጥረትም ኢትዮጵያ ከኬንያ የተሻለ ደረጃ ላይ ነች። የኬንያ የምግብ እጥረት መጠን 36.8 በመቶ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ደግሞ 19.7 በመቶ ነው።

በጥቅሉ ሲታይ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ንጽጽር፣ ወጥ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ አያስደፍርም። ኬንያ ትልቅ ኢኮኖሚ፣ ከፍተኛ የነፍስ ወከፍ ገቢ እና ትልቅ በጀት ቢኖራትም፣ ከፍተኛ የዕዳ ጫና ውስጥ ነች። ከኬንያ አንጻር ዝቅተኛ የእዳ ጫናና አነስተኛ አመታዊ በጀት ያላት ኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ላይ መሆኑ አይኤምኤፍ መረጃ ያመለክታል።
የዓለም የረሃብ መለኪያም ኬንያን ከኢትዮጵያ በትንሹ ዝቅ ያለ ደረጃ ላይ ያስቀምጣታል። ከሁሉም በላይ የበጀት መጠን ብቻውን የአንድን ሀገር ኢኮኖሚያዊ ጥንካሬ ወይም አፈጻጸም ለመለካት በቂ አይደለም።












