Loading...

አሜሪካ ፕሬዝደንት ማዱሮንና ባለቤታቸውን እንድትለቅ ቻይና ጥሪ አቀረበች

አሜሪካ ባለፈው ቅዳሜ በቬኔዙዌላ ዋና ከተማ ከራካስና በወታደራዊ ካምፖች ላይ 150 ጄቶችን ያሳተፈ መጠነሰፊ ጥቃት በመክፈት ፕሬዝደንት ኒኮላስ ማዱሮንና ባለቤታቸውን በቁጥጥር አውላ ወደ ኒው ዮርክ መውሰዷ አለምን አነጋግሯል።

ድፍረት የተሞላበት ይህ የአሜሪካ እርምጃ አለምን በድጋፍ፣ በተቃውሞና በዝምታ በሶስት ጎራ አስልፏል።

ቻይና፣ አሜሪካ የሉአላዊ ሀገርን ፕሬዝደንት መያዟን ከተቃወሙት ሩሲያና ብራዚልን ከመሳሰሉት ጥቂት ሀገራት ዝርዝር ውስጥ ተካታለች። አብዛኞች ሀገራት ከአሜሪካ ጋር ባላቸው ቅርበት ወይም ላለማስከፋት በሚል የማዱሮን መያዝ በዝምታ ሲመለከቱ ሌሎች ጥቂቶች ደግሞ የአሜሪካን እርምጃ ትክክለኛ ነው በሚል ድጋፋቸውን ገልጸዋል።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በትናንትናው እለት አሜሪካ በቁጥጥር ስር ያዋለቻቸውን ማዱሮንና ባለቤታቸውን ባስቸኳይ እንድትለቅና የቬኔዙዌላን መንግስት ለመገርሰስ የምታደርገውን ጥረት እንድታቆም ጥሪ አቅርበዋል።
ቃል አቀባዩ አክለውም የአሜሪካ እምርጃ የአለምአቀፉ ህግን፣ የአለምአቀፉ ግንኙነት መሰረታዊ ባህሪያትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተር መርሆዎችን በግልጽ የሚጥስ ነው ብለዋል።

ቆየት ብሎ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ይ ከፓኪስታን አቻቸው በቤጂንግ በሰጡት መግለጫ አሜሪካን ባይጠቅሱም ከዚህ በኋላ “የአለም ዳኛ” ለመሆን የሚሞክር ሀገርን እንደማትቀበል ተናግረዋል።

ዋን ይ ከማዱሮ መያዝ በኋላ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት “በአለምአቀፍ ህግ መሰረት የሁሉም ሀገራት ደህንነትና ሉአላዊነት መከበር አለበት።”

አሜሪካ ማዱሮን የያዘችው፣ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ማዱሮ ወደ አሜሪካ አደንዛዥ እጽ ለሚያዘዋውር ወንጀለኛ ቡድን ሽፋን እየሰጡ ነው በሚል ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ካሰሙ በኋላ ነው።

በቁጥጥር ስር የዋሉት ማዱሮ ከእጽና ጦር መሳሪያ ጋር የተያያዘ ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን በዛሬው እለት በኒው ዮርክ በሚገኘው ፍርድ እንደሚቀርቁ ይጠበቃል።

Share this article

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው