ናይጀሪያና አሜሪካ በቻድ ሀይቅ ተፋስስ ባካሄዱት የጋራ ወታደራዊ ዘመቻ አቡ ቢላል አል ሚኑኪ የተባለውን የአስላሚክ ስቴት(IS) ከፍተኛ አዛዥ መግደላቸውን አስታውቀዋል።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሚኑኪ ከአለምአቀፍ የአይኤስ ከፍተኛ አዛዦች መካከል አንዱ እንደሆነ ሲገልጹ የናይጀሪያው ፕሬዝዳንት ቦላ ቲኑቡ ደግሞ ጥቃቱ በታጣቂ ቡድኑ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ያደረሰ ነው ብለዋል።
እንደ ቢቢሲ ዘገባ ከሆነ አይኤስ በምስራቅ አፍሪካ ከሚያካሂዳቸው ዘመቻዎችና እአአ በ2018 ከተፈጸመ የዳፕቺ ሴት ተማሪዎች እደገታ ጀርባ እጁ እንደነበረበት የገለጸው የቀድሞው የቦኮሀራም አዛዥ ሚኑኪ ከበርካታ ወራት አሰሳ በኋላ ከበርካታ ረዳቶቹ ጋር በቦርኖ ግዛት በሚገኘው ጠንካራ ምሽግ ላይ በተወሰደ የአየር ጥቃት ተገድሏል። የቦኮሀራምና የአይኤስ ታጣቂ ቡድኖች በዋናነት የሚንቀሳቀሱት በቻድ ሀይቅ ተፋሰስ ነው።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ እንዳሉት የአዛዥ መገደል የአይኤስን የአፍሪካና የአለምአቀፍ ትስስር የሚበጥስ በመሆኑ የፋይናንስ ፍሰቱንና የእዝ ሰንሰለቱን የሚያዛባ ነው።
ለዘመቻው መሳካት የናይጄሪያ መንግስትን ያመሰገኑት ትራምፕ ሚኑኪ “ከዚህ በኋላ ህዝብ አያሸብርም፣ አሜሪካውያን ኢላማ ለሚያደረግ የዘመቻ እቅድም እርዳታ አያደርግም” ብለዋል።
ናይጄሪያና አሜሪካ፣ ናይጄሪያን ከአስርት አመታት በላይ ያመሳትን የአክራሪዎች ጥቃት ለማስቆም ወታደራዊ ትብብራቸውን እያሰፉ ናቸው።
በሩዋንዳ ኪጋሊ በተካሄደው የዋና ስራ አስፈጻሚዎች ስብሰባ ላይ የተገኙት ፕሬዚዳንት ቲኑቡም የደህንነት ስጋትን በብቸኝነት መቅረፍ እንደማይቻል በመግለጽ ከአሜሪካ ጋር ያለውን አጋርነት አስፈላጊነት ተከላክለዋል።
ቀደም ሲል የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ናይጀሪያ ታጣቂዎች በአናሳዎች በተለይም በክርስቲያኖች ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት ማስቆም አልቻለችም የሚል ጠንካራ ክስ ማሰማታቸው ይታወሳል። ትራምፕ ናይጄሪያ ጥቃቱን ካላስቆመች፣ አሜሪካ ወታደራዊ እርምጃ እንደምትወስድም አስጠንቅቀው ነበር። የናይጄሪያ መንግስት ጥቃት ሀይማኖት የለየ አይደለም በማለት ነበር ክስሱን ያጣጣለው።
ነገር ግን አሁን ላይ ሁለቱ ሀገራት የጋራ ወታደራዊ ጥምረት በመፍጠር በናይጄሪያ በሚገኙ ታጣቂ ቡድኖች ላይ እርምጃ እየወሰዱ ይገኛሉ።











