የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ያስተላለፉትን አዲስ መመሪያ ተከትሎ አገሪቱ “አባካኝ፣ ውጤት የለሽ እና ጎጂ” ካለቻቸው 66 ዓለም አቀፍ ተቋማት እና ስምምነቶች ራሷን ማግለሏን በይፋ አስታውቋል። ይህ ታሪካዊ ውሳኔ የተላለፈው ተቋማቱ ከአሜሪካ ብሔራዊ ፍላጎት ጋር የሚቃረኑ እና የታክስ ከፋዩን ገንዘብ ያለምንም ውጤት ለውጭ አጀንዳዎች የሚያውሉ ሆነው በመገኘታቸው እንደሆነ ተገልጿል። የአሁኑ የትራምፕ አስተዳደር እነዚህ ድርጅቶች በስርዓት የማይመሩ፣ ደካማ አስተዳደር ያላቸው እና የአሜሪካን ሉዓላዊነትና ነፃነት የሚጋፉ መሆናቸውን በመግለጫው አጽንቷል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በሰጡት ግልጽ ማብራሪያ የአሜሪካ ህዝብ ደም፣ ላብ እና ውድ ሀብት ያለምንም ፋይዳ ለውጭ ጥቅም የሚፈስበት ጊዜ ማብቃቱን ገልጸው፣ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር የታክስ ከፋይ ገንዘብ በህዝቡ ወጪ ለባዕዳን አጀንዳ ማስፈጸሚያነት መዋል የለበትም ብለዋል። በመሆኑም አሜሪካ ከተወሰኑ የተባበሩት መንግስታት ድርጅቶች የምትወጣ ሲሆን ስትሰጥ የቆየችውን የገንዘብ ድጋፍም ወዲያውኑ እንደምትቋርጥ አስታውቃለች። በተጨማሪም አሜሪካ ለማንኛውም ዓለም አቀፍ ድርጅት የምትሰጠው ድጋፍ ወደፊት ዳግም እንደሚገመገም ተመልክቷል።
በጥቁር መዝገብ ውስጥ ከተካተቱት 66 ተቋማት መካከል በአዲስ አበባ መቀመጫውን ያደረገው የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን (ECA) እና ሌሎች ክልላዊ የኢኮኖሚ ኮሚሽኖች ይገኙበታል። በተጨማሪም የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፍ ስምምነት (UNFCCC) እና በይነ መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ፓነል (IPCC) ከአሜሪካ የገንዘብና የዲፕሎማሲ ድጋፍ የተሰረዙ ዋነኛ ተቋማት ናቸው። እንደ ስቴት ዲፓርትመንቱ ገለጻ ከሆነ እነዚህ ተቋማት ለሰላምና ለትብብር የተመሰረቱ ቢመስሉም፣ በተግባር ግን በተራማጅ ርዕዮተ ዓለም የሚመሩ እና ከአሜሪካ ብሄራዊ ጥቅም የተነጠሉ ሆነው ተገኝተዋል።
መግለጫው አክሎም እነዚህ ተቋማት ከስርዐተ-ፆታ እኩልነት ዘመቻዎች እስከ አየር ንብረት አስተምህሮዎች ድረስ ያሉ የሉላዊ ፕሮጀክቶች አስፈጻሚዎች መሆናቸውን ጠቅሷል። አሜሪካ ከጥቅሟ ጋር ተያያዥነት በሌላቸው ወይም በሚጋጩ ተቋማት ውስጥ የምታፈሰውን ሀብት እና የዲፕሎማቲክ ካፒታል እንደማትቀጥል በማሳወቅ፣ ህዝቧን በሚጠቅም ቦታ ላይ ብቻ ትብብር እንደምትሻ አሳውቃለች። ይህ እርምጃ አሜሪካ ለዓመታት የገነባችውን ዓለም አቀፋዊ የNGO መረብ እና የዩኤስኤአይዲ (USAID) አሰራርን የማፍረስ አካል ተደርጎ ተወስዷል።











