በኢራን የቀጠለው ህዝባዊ አመጽ አስራ ሶስተኛ ቀኑን የደፈነ ሲሆን እስካሁን የሟቾች ቁጥር ከ40 በላይ መድረሱ በበርካታ የዜና ምንጮች ተዘግቧል።
የትራምፕን ሰሞንኛ የኢራን መንግስት ላይ ያነጣጠሩ ዛቻዎችን የሚደግፋ የፖለቲካ ታዛቢዎች የኢራንን አገዛዝ ለመጣል ከአመታት በኋላ እጅግ አመቺው አጋጣሚ መፈጠሩን ያመላክታሉ። የትራምፕ አስተዳደር በኢራን የተፈጠረውን ውስጣዊ ነውጥ በማቀጣጠል አገዛዙ እንዲወድቅ ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ይጠቁማሉ።
ለኢራናውያኑ ነጻ የኢንተርኔት እና VPN አገልግሎት ማቅረብን የመሳሰሉ ወሳኝ አገልግሎትን ማቅረቡ የመንግስቱን ፍጻሜ እንደሚያፋጥነው ይገልጻሉ።
የመንግስቱ የበላይ መሪ(Supreme leader) አያቶላህ አሊ ሃሜኔይ ተቃውው ኢራንን ለማፍረስ በሚሰሩ የውጭ ሃይላት እንደተቀነባበረ የተናገሩ ሲሆን ጣቶቻቸውን ዶናልድ ትራምፕ እና የቀድሞው የኢራን ዘውዳዊ ገዢ ቤተሰብ ላይ ይቀስራሉ። “ለውጭ ኃይል አገልጋይ የሆነ ሰው ቅጥረኝነቱ ለውጭ ኃይል እንደሆነ ሰዎች ያውቁታል፣ እስላማዊ ስርዓቱ ለይቶ ያውቀዋል።” ሲሉ በቀጥታ በአሜሪካ ድጋፍ ስልጣኑን ዳግም ለመቆናጠጥ ያሰበው የቀድሞው የኢራን ዘውዳዊ ቤተሰብ የመጨረሻው ሻህ፥ ሬዛ ፓላቪ ላይ ያነጣጠረ ንግግራቸውን አድርገዋል።
ኢራን በአገር ውስጥ ችግር የተጠመደች ቢሆንም የብሪክስ ፕላስ የባህር ኃይል ወታደራዊ ልምምድን ለማድረግ የጦር መርከቧን በደቡብ አፍሪካ የባህር ክልል ላይ ከሩሲያ እና ቻይና ጎን ይዛ ቀርባለች። ታዛቢዎች የኢራን አገዛዝ በአስራ አንደኛው ሰዓቱ ላይ እንደሆነ ቢጠቁሙም፥ በውጥረቱ መሃል መንግስቱ የአለም አቀፋዊ የሃይል አሰላለፍ ፉክክሩ ላይ ተሳትፎውን ቀጥሏል።













